Wednesday, October 23, 2013

የለውጥ ጅማሮ

        (ዓለምነው ሽፈራው፡ ጥቅምንት 14 ቀን 2006 ዓ.ም.) ፦ ለውጥ የተጀመረ ይመስለኛል።  ላለፉት ጥቂት አመታት ወርኃ ጥቅምት እና ሚያዚያ ወይም ግንቦት ሲደርስ አንዳንድ የሁሉንም ክርስቲያን ቀልብ የሚስቡ፣ የሚያስደስቱ፣ ከዚያ በተቃራኒው  የሚያናድዱ ነገሮች መስማት የተለመደ ነበር።   ነገሩ እንዲህ ነው።
የስዕል ምንጭ፡ ማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር 
በኢ.ት.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የቤተክርስቲያኗ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደርጋቸው ሁሉት አመታትዊ   ጉባኤያት የሚካሄዱት በነዚህ ወቅቶች ነው።  እነዚህ ጉባኤያት ቤተክርሲቲያኗን የተመለከቱ መንፈስዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባቸው ናቸው።  ውሳኔዎቹም ይግባኝ የሌላቸው ናቸው። ምክንያቱም የሚወስናቸው የቤተክርስቲይኗ የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነውና።   ልክ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥቅምት እና ሚያዚያ ወይም ግንቦት ላይ ጉባኤውን  ሲጀምር እውነተኛውም ሐሰተኛውም መረጃ እንዳደርሳለን ባይ ጡመራ በሙሉ ስራውን አጧጡፎ ይጀምራል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በጸሎት ጉባኤውን ሲከፍት፣ በጸሎት ከፈተ፤ አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ ሲሰይም፣ አጀንዳ  አርቃቂ ኮሚቴ አቋቋመ፤ አንጀንዳዎች ሲለዩ፣ እነዚህ አጀንዳዎችን መርጧል፣ እነዚህን አልመረጠም፤ ወ.ዘ.ት. በማለት ይጀምራሉ። ከዚያም ገና የጉባኤው የመጀመሪያ እለት ላይ ብጹዕ አቡነ እገሌ እንዲህ ብለው፣ ብጹዕ አቡነ እገሌ እንዲህ ብለው አቡነ እገሌ ገስጿቸው፤ ብጹዕ አቡነ እገሌ እንዲህ አርድገው እንዲህ ተባሉ  ወ.ዘ.ተ.... በማለት ይቀጥላሉ። እንዲህ እያሉ የሲኖዶሱን ስብሰባ በሙሉ እውነቱንም ወሸቱንም፣ የተባለውንም ያለተባለውንም ሲያጎርፉት ጦማሪዎች አብረው ከሲኖዶሱ ጋር አብረው የሚሰበሰቡ ይመስል ነበር። ይህንን ተከትሎ የህዝበ ክርስቲያኑ ልብም አብሮ ከወዲያ ወዲህ ሲል ሲብከነከን ይሰነብታል።   አይ ለምን አባ እገሌ እንዲህ አሉ? አባ እገሌስ እንዲህ ያሉት ለንምድን ነው? እንዲህ ማለት ነበረባቸው፤ ኤጭ እሳቸውማ ልማዳቸው ነው፤ እንዲህ ብለው መናገር ነበረባቸው፣ ሲኖዶሱ እንዲህ ብሎ መወሰን ነበረበት፣ ወ.ዘ.ተ. በማለት  እነዚህ መከረኛ አባቶች በክፉም በደጉም ሲቦጭቃቸው ይውላል ያድራል። ሥራው ሁሉ ስለሲኖዶሱ ጉባኤ ማሰብ ብቻ ይሆናል።  «ሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማኀበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ አንተ ግን ሥራህን ሥራ!» እንዳሉት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ፤ ሥራ መስራቱን ትቶ ሁሉም ስለ  ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሎ ወሬ ለቀማ ሲጣደፍ ይስተዋል ነበር። ሥራውን መሥራት ትቶ ጉዳዩ የሚያገባው ቢሆንም ሲኖዶሱ ውስጥ ገብቶ መወሰን የማይችለውን፤ ጉዳዩ የሚመለከተው ቢሆንም ገብቼ አንድ የሲኖዶ አባል ተሰብሳቢ ልሁን ብሎ ማመልከቻ ማስገባት የማይችለውን፣ እንዲሁ በሚያገባውም፣ በማያገባውም፣ በሚመለከተውም፣ በማይመለከተውም የራሱንም አዕምሮ  ሲያስጨንቅ እድሜውን ይገፋል። ከነዚህ ውስጥ እኔም አንዱ ሰለባ ነበርኩ። የእሱ ሃሳብ አባ እገሌ ተናገሩት፣ ወይም  ሲኖዶሱ  የሱን ሃሳብ የሚቀርብ ወሰነ ሲባል ደስ የሚለው፤ የእሱን ተቃራኒ አባ እገሌ ተናገሩ ሲባል በእኒያ አባት ላይ የሚያጉረመርም፤ የእሱን ሃሳብ  የመሰለ ሃሳብ በሲኖዶሱ ጉባኤ ውስጥ ተነስቶ ተቀባይነት አጣ ሲባል ሲኖዶሱ መንፈስ ቅዱስ ርቆታል እስከ ማለት የሚደርስም ብዙ ነው። ወ.ዘ.ተ.

መረጃ በጊዜው ለሚመለከተው አይድረስ አልልም። መድረስም አለበት። ሰውም መረጃን መፈለጉ ክፉት የለውም፤ ነገር ግን መረጃው ለምን፣ ከማን፣ እንዴት እና መቼ የሚሉት ጉዳዮች ወሳኝነት አላቸው። የቤተክርስቲያኗን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በተለይም ወሳኝ የሆነውን የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ  መረጃ ግን ቤተ ክርስቲያኗ በኦፊሲያል  እንደየ አስፈላጊነቱ (ለህዝበ ክርስቲያኑ መነገር የሚገባውን) ማድረስ ግዴታዋም ነው፤ ኃላፊነትም አለባት። ይሁን እንጂ  እውነት ይሁን ሐሰት ማጠራት እንኳን በማይቻልበት፤ ማን እንደሚጽፈው በማይታውቅበት፤ የመረጃው ምንጭ ከየት እንደሆነ ሳይታወቅ የቤተ ክህነት ምንጮቻችን እንደነገሩን እየተባለ በድብቅ በሚጻፍበት ዘመን  መረጃውን ቀድመን  በስማ በለው ከሚሰሙት ጦማሪዎች  መስማት የለበትም።  ህዝቡም በመረጃ ሲጭበብረበር፣ ሲምታት ዘመኑን ሙሉ መኖር የለበትም።  የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ወቅቱ በሚፈቅደው ሁሉ መረጃውን ለልጆቿ ብታደርስ፤ ጳጳሳቱም አይሰደቡም፣ ቤተ ክህነቱም አይነቀፍም ነበር። እንደአለመታደል ሆኖ እስከአሁን ይኼንን ሲሰራበት አላየንም። ዛሬ ግን ለውጥ የተጀመረ ይመስለኛል።

እንደተለመደው ሁሉ የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከተጀመረ ሁለት ቀናት አስቆጥሯል። በመጀመሪያው እለትም የጉባኤውን መጀመር አስመልክቶ  ቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ማንነታቸው የሚታወቁ የዜና ምንጮችም ሆነ በድብቅ የሚጽፉ ጦማሪዎች መረጃውን አድርሰውናል። በቤተክርስቲያኗም ድረ ገጽ ላይ መረጃው ለሁሉም በይፋ ተለጥፏል።  ይህ በጣም አስፈላጊና ተገቢ ነው። ይበልም ያስብላል። ከዚህ ያለፈ መረጃ እስከ አሁን አላየሁም።  የለውጥ ጅማሮው አንድ እርምጃ ይኼ ነው።

ሌላኛው ከዚህ በፊት የሚደረጉትን ጉባኤያት መረጃ አንድ በአንድ እውነትም ይሁን ሐሰት ሳይጣራ፤ ውሳኔ ይሁን ሀሳብ ሳይታወቅ፤ አንዱ ሊቀ ጳጳስ ያነሱትን ሃሳብ የቅዱስ ሲኖዶዱ ውሳኔ ይሁን የሊቀ ጳጳሱ የግል ሃሳብ ሳይለይ እንዲሁ  በጅምላ የጠዋቱን ከሰዓት፣ የከሰዓቱን ውሎ በአመሻሽ እንዲሁ እንደወረደ ይበትኑት ነበር። መረጃው ከየት፣ በየት፣ እንዴት፣ መቼ፣ ለምን እንደወጣ እንኳን ምንም አይነት ማስረገጫ የለም። ብቻ ጦማር ላይ ይከተባል፣ አድሜም ያነባል፣ እንደፈለገው ይተረጉማል፣ የፈለገውንም ያደርግ ነበር። በዚህ ላይ ሁሉት ነገሮች ይታዩኛል። አንድ ጦማሪያኑ ይህንን ያልተሟላ፣ ያልተጣራ መረጃ ከየት ነው የሚያገኙት? ጦማሮያኑ የሲኖዶሱ አባላት ናቸውን ያስብላል። ወይንስ የሲኖዶሱ አባላት ወደ ስብሰባው ሲገቡ ስልካቸውን ከፍተው ከጦማሪያኑ ጋር ሲነጋገሩ ነው የሚውሉት? ወይንስ ጦማሪያኑ የሲኖዶሱ አባላት የሚያስቡትን እና የሚናገሩት የመገመት፣ የመተንበይ ሃብተ ትንቢት ተሰጥቷቸዋል?  ወይንስ ቤተ ክርስቲያኗ ለድብቅ ጦማሪዎች ብቻ መረጃውን በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው፣ በየቅጽበቱ ታደርስ ነበር? በእርግጠኝነት የመጨረሻውን  ቤተ ክርስቲያኗ አታደርግም። እንዲደረግም አትፈቅድም።  ታዲያ የመረጃው ምንጭ ከየት ነበር? መልሱን ለጦማርያኑ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ትቸዋለሁ።  ሁለት የቤተክርስቲያኗ አስተዳደር ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለምዕመኑ በጊዜው የማያደርስበት ምክንያቱስ ምን ነበር? የማስተላለፊያ አቅም ጠፍቶ? ዘመኑ መረጃ ለማዳረስ ከባድ ሆኖ? ወይስ መረጃው ለምዕመናኑ መድረሱ የማያስፈልግ ሆኖ ነውን? ወይስ ያልታወቀ ምክንያት ነበር? መልሱን ከእኔ ይመስለኛል ግምት ይልቅ  ከቤተክህነቱ እና ከሲኖዶሱ አባላት መስማት ይሻላል።

በአሁኑ ጉባኤ  ግን ይኼው አርባ ስምንት ሰዓት አለፈ አንድም ስለሲኖዶሱ ስብሰባ መጀመሩን ከማብሰር  ውጭ የተባለም፣ የተነገረም፣ የተጻፈም ነገር አላየሁም፤ የለም።  ለዚህስ ምክንያቱ ምን ይሆን?  ጥቂቶቹ ግሞቶች እነዚህ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ስለውሏቸው በየሰዓቱ ለጦማርያን መረጃ ከመስጠት ይልቅ ወደ ጉባኤያቸው ያተኮሩ ይመስለኛል። የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የውሉ ዘገባ የሚጻፍለት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ውሳኔ የሚወሰንበት ነውና። አንድም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ አንገብጋቢ የሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች የሉም ብሎ በማሰብ ጦማርያኑ ከቤተ ክህነቱ ራቅ ብለው ይሆን? ይህ ነው እንዳይባል በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ውስጥ በአስቸኳይ መፈታት የሚያስፈልጋቸው አያሌ የሆኑ አንገብጋቢ ውስጣዊ እና ውጫው ጉዳዮች አሉ። እነዚህን አይደለም አይን ያለው፣ አይነ ስውርም ያያቸዋል፤ አይደለም ጆሮ ያለው፣ ደንቆሮም ይሰማቸዋል።  አንድም ቤተክርስቲያኗ የግባኤዬን መረጃ እንደፈለጋችሁ እየቆነጻጸላችሁ፤  «መጣሁልሽ» እያለች ጩኸት እንድምታበዛ ቀበሮ በጎቼን አታስጨንቁ፤ እነሱም ሥራቸውን ይስሩበት፤ እናንተም ስራችሁን ፈልጉ፤ ብላ መረጃው ከጉባኤው እንዳይወጣ ወስና ይሆን። እነውነት ነው የቤተክርስቲያንን መረጃ ቤተክርስቲያን ስታውጀው እንጂ በስማ በለው ሲሰማ ለጆሮ አይጥምም። አንድም ጦማርያኑ የሚጦምሩበት በይነ መረብ አገልግሎቱን አቁሞ ይሆን? እዲህ እንዳንል ብዙዎቹ የሚጠቀሙበትን ይኼው እኔ አሁን ይህንን ጽሑፍ እየከተብኩበት ነው።   አንድም የሲኖዶሱ ስብሰባ በአንድ ቀን ተፈጽሞ ይችል ይሆንን። ይህ ቢሆንም ቢያንስ መፈጸሙ ሳንሰማ አንቀርም ነበር። ታዲያ ለምን ይሆን ስለሲኖዶስ ስብሰባ አንድም ሳንሰማ አርባ ስምንት ሰዓት የሞላው? እንደ እኔ የለውጡ አንዱ እርምጃ  ነው ባይ ነኝ። የቤተ ክህነቱ አስተዳደር ለምን መረጃውን በጊዜው አላደረሰንም የሚል ሃሳብ ይነሳ ይሆናል። ያደርሰናል ብለን እንጠብቅ። እንዲያው በየቀኑ የተባለውን ሁሉ የሚናገር ከሆነማ ምኑን ከድብቅ ጦማሪያን ተሻለ? ሃሳቡስ መቸ ተነስቶ፣ መቼ ምልዓተ ጉባኤው ተወያይቶበት ውሳኔ ሰጠበት ይበለን? «ከረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል» እንደሚባለው ረጋ ብሎ መረጃውን ሊያደርሰን ይገባል። ቤተ ክህነቱ ይህንን እንደሚያደርግም ተስፋ አለኝ። ለውጡም እንደሚቀጥል ተስፋዬ ሙሉ ነው።

ባለፈው አመት የካቶሊካዊያን ቤተክርስቲያን ፖፕ (እንደ ፓትርያርክ ማለት ነው) ስልጣን በቃኝ፣ ኃላፊነት በዛብኝ ብለው ስልጣናቸው ለሰጣቸው የቤተክርስቲያናቸው አስተዳደር በአጭር ጊዜ ውስጥ አስረክበዋል። ምንም እንኳ በእምነት ባይመስሉንም አስተዳደራቸውን እንደምሳሌ ብንወስደው አይከፋም።  «የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች» እንዳትሉኝ። «መልክ ስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ» አይደል ብሂሉ። ቅድስት ተዋህዶ  እምነታችንን ይዘን አስተዳደርን ከጎረቤት ብንማር ክፋት የለውም ነበር።
የቤተክርቲያኒቱ አስተዳደርም ተተኪውን ፖፕ ለመምረጥ ሲዘጋጅ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሳለፈው በኋላ የምርጫው እለትም ደረሰ። የምርጫው ሂደት በእጅጉ  የሚያስቀና፣ የእምነቱን ተከታይም የሚያጓጓ፣ የሚያኮራም ነበር። የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንንም ቀልብ የገዛ ነበር። ምርጫው የተደረገባትን የቫቲካን ግዛት፣ የሮምን ከተማም ማን ይሆን በሚል ጉጉት ያስጨነቀም ነበር። ምርጫው በሚደረግበት ወቅት መራጮች ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ  ከማንም ሰው ጋር አልተናኙም። በነገራችን ላይ በካቶሊክ ቤተከርስቲያ የፖፕ መራጮች እና ተመራጮች  ካርዲናሎች ማለትም ጳጳሳት ብቻ ናቸው። ከውጭው ህዝብ ማለትም ከእምነቱ ተከታዮች እና ከመገናኛ ብዙኃኑ ማኅበረሰብ ጋር የሚገናኙት እና የሚግባቡት  በ«ጭስ» ምልክት ብቻ  ነበር። ፖፑ ሲመረጥ የጭሱን መልክ የተለየ በማድረግ መመረጡን ያበስራሉ። ፖፑ በአንድ ቀን ባይመረጥ ለብዙ ቀናት ይህ ሁኔታ ይቀጥላል። ፖፑ እስከመረጥ ድረስ ማለት ነው።  ከዚያ በኋላም  መራጮች ከውጪው ማኀበረሰብ ጋር መገናኜት ይችላሉ። መራጮችም መገናኛ ብዚኃንም የፈለጉትንም መናገር ይጀምራሉ። እስከዚህ ሰዓት ድረስ ግን ማን እንደሚመረጥ፣ ማን እጩ እንደሆነም ማወቅ በፍጹም አይቻልም።

የካቶሊካዊያኑን  አስተዳደር ማንሳት የፈለግኩበት እና በእኛ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ መሆን ያለበት አንድ ጉዳይ  አለ። ያም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጉባኤ ሲጀመሩ ጉባኤው እስኪፈጸም ድረስ ከምዕመናን እና ከውጭው ማኅበረሰብ  ከመገናኛ ብዙኃን  ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ ቢቻልም ፈጽሞውኑ ማስቀረት ነው። ሲኖዶስ ስብሰባ ተሰብስቦ የዋለን አንድ የሲኖዶስ አባል ከስብሰባ ሲወጣ መረጃ ስጠን ብሎ በማጣደፍ፣ የሲኖዶሱን አካሄድ በመገምገም የዚያንንም የሲኖዶስ አባል ሃሳብ መቀልበስ እና በቀላሉ መለወጥ ይቻላል። ምክንያቱን የሲኖዶሱ አባላት ጳጳሳት ቢሆኑም እንኳ ሰው ናቸው እና ሊሳሳቱ፣ ሊታለሉ ይችላሉ። ለዚህ ዋነኛው  መፍትሄ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ወቅት  የሲኖዶሱን አባላት  ከሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ ነው። ለመገናኛ ብዙኃን ወይንም ለምዕመናን መረጃ ለማድረስም ራሱ ሲኖዶሱ የሚመልከተውን አካል ወይንም የሲኖዶስ አባል ሊሰይም እና መረጃ እንዲያደርስ ቢያደርግም መልካም ነው።  ይህ ከሆነ የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ወጤታማ፣ ውሳኔውም ርቱእ ይሆናል። ካህናቱና ምዕመናንም ውሳኔውን አሜን ብሎ በመቀበል ለተግባራዊነቱ ይጥራሉ።

እግዚአብሔር አምላክ ለአባቶቻችን ስለቤተ ክርስቲያን መልካም ነገር የሚወያዩበት፣ የሚወስኑበትን አቅሙን፣ ጸጋውን ያድልልን። የአባቶቻችን በረከት ይደርብን።  አሜን።

ቤተክህነታችን ሆይ ትንሳኤህን ያሳየን!!!
ሃይደልበርግ፣ ጀርመን!

1 comment:

  1. ወንዲሜ አለምነው
    ይህን ለብዙ ጊዜ የቆየ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መረጃን በጊዜውና እውነታውን እንደጠበቀ ያለማድረስ ችግር ፣ ተያይዞም የሃይማኖቱ ተከታዮች ማግኘት የሚገባቸውን መረጃ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ሲፈጠር የቆየውን ምስቅልቅል ያየህበትና የገለጽክበት መንገድ በጣም ደስ ይላል ። እየታየ ያለውንም ጭላንጭል ተስፍ እኔም እጋራለሁ። ሁሉም የቤተክርስትያኗ ልጆች በእምነቲቷ ስም ከመጠራት በዘለለ ስለቤተክርስትያን ሁኔታ ግድ ቢላቸው ለውጡ እሩቅ አይሆንም።

    ReplyDelete