Monday, August 19, 2013

የነሐሴ ወር የልጅነት ትዝታዎቼ!

    (ዓለምነው ሽፈራው:) ልክ ወርኃ ነሐሴ ሲብት (ሲጀምር) ከሁሉም የማልረሳቸው የሴት አያቴ የምለላ (የልመና) ግጥሞች ትዝ ይሉኛል። በዚህም የተነሳ መሃላዬን አስፈትቶ ዛሬ ወደ ፌስ ቡክ ዓለም ዘልቂያለሁ። 

ሁሉም ሰው ከዓመታት፣ ከወራት፣ ከሳምንታት፣ ከእለታት እንዲሁም ከበዓላትና ከአጽዋማት ዘንድ በጣም አብዝቶ የሚወዳቸው እና ብዙም ትዝታ ያሳለፈባቸው የየራሡ ጊዜያት  እንደሚኖሩት ጥርጥር የለኝም። ለምሳሌ ያክል በእኛ በኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች ዘንድ በልጅ አዋቂ የምትወደደው፤ መቼ መጣች ተብላ የምትጠበቀው፤ የፍልሰታ ጾም አንዷ ናት።  ለእኔም በልጅነት አእምሮዬ ብዙ ትዝታን ጥለው ካለፉት ጊዜያት የፍልሰታ ጾም አንዷ እና የመጀመሪዋ ነች። ነገሩ እንዲህ ነው። 

ምድር ይቅለላትና፣ ነፍሷንም ይማረውና የሴት አያቴ (የአባቴ እናት) የፍልሰታን ወርህ በልዩ ምለላ (ልመና) ታሳልፍ ነበር። እንኖርበት የነበረው (አሁንም ወላጆቼ የሚኖሩበት)  ቦታ ገጠር እንደመሆኑ መጠን አብያተ ክርስቲያናቱን እንዲሁ በቀላሉ ማግኜት ጉልበት ላለው ካልሆነ በቀር ለአቅመ ደካማ (ህጻናትን ጨምሮ) የሚቀመስ አይደለም። አያቴም እድሜዋን ያገባደደች ስለነበረች ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ አቅም አልነበራትም። እንደ አጋጣሚም ሆነ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ከእኛ የመኖሪያ ቤት ለጠንካራ ተጓዥ ከአንድ ሰዓት ከሩብ በላይ በእግር ያስሄዳል። በዚህም የተነሳ ከእናቴ ጀርባ ከወረድኩበት እለት (በሦስት ዓመት እድሜዬ አካባቢ) ጀምሮ ከአንድ ሰዓት በላይ የመጓዝ አቅም እስከአገኘሁበት ቀን (ከስምንት ዓመት አካባቢ ሲሆነኝ) ድረስ በአንዳንድ ታላላቅ በዓላት ካልሆነ በቀር በንጋት ይሁን በጠዋት፣ በቀትርም ይሁን በሰርክ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ አልነበረም። የልጅነት ጊዜዬን ፍቅር ብቻ ከነበረች አያቴ ጋር  አሳልፍ ነበር።  ታዲያ ያኔ በተለይ በወርኃ ነሐሴ በፍልሰታ ጾም  እና በእለተ ሰንበት እናቴም አባቴም ሁሌ ወደ ቤተክርስቲያን ስለሚሄዱ፤ ከእድሜ እኩያቶቼ ጋር ሆኜ  ጉደኛዬም፣ እናቴም አባቴም አያቴ ነበረች። ያን ጊዜ  ነው እንግዲህ አያቴ በጾመ ፍልሰታ የማይረሳ ትዝታ ጥላልኝ ያለፈች።

ምንም እንኳን ልጅ ሆኜ ለምን እንደምታደርገው ባይገባኝም፤ መቁጠሪዋን እየቆጠረች ብዙ ስትጸልይ አያት ነበር። ለእኔም አቡነ ዘበሰማያትን ያን ጊዜ አስተማረችኝ። ይህም ብቻ አይደለም። በተለይ ከሁሉም ጊዜ በበለጠ በጾመ ፍልሰታ ወቅት ደግሞ  አያቴ ታደርጋቸው  የነበሩት ሁኔታዎች  ያኔ በልጅነት አእምሮዬ እጅጉን  ይማርኩኝ ነበር። በተለይ ማታ ማታ ከመተኛቷ በፊት ደስ በሚል የባልቴት (የተከረበች አዛውንት እናት ማለት ነው) ድምጽ እያዜመች፣ ልዩ ልዩ ጣዕም ያላቸውን ግጥሞች ታሰማን ነበር። እኔ ያኔ የማውቀው ስለእመቤታችን  ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ መሆኑን ነበር። ያን ጊዜ እኔ ግጥሙን ለመስማት እንጂ ትርጉሙና ምስጢሩ ላይ ትኩረቱ አልነበረኝም።  በግጥሙ እና ዜማው ውሳጠ መንፈሴ ደስ ይሰኝ ስለነበር ብቻ ዘወትር ከእሷ ጋራ እያደርኩ ምለላውን እሰማ ነበር። ከብዙ የግጥሞቿ ስንኞች መካከል አንዱ ይህ ነበር፡
«ከሁሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች፤
ከጭቃ ወድቃ ትነሳለች፤
ገለባ ለብሳ ትገኛለች።
ከዚያች ጤፍ፤
የአዳም ልጅ ሁሉ አትስነፍ። 
የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና፤
የሰማይ ቤቱን ረሳና፤
በላው ዲያቢሎስ ወሰደና። 
አንተ የአዳም ልጅ ተው አትስነፍ፣ ተው አትዘንጋ፤
ተሰርቶልሃል የእሳት አልጋ። 
የእሳት አልጋ የእሳት ባህር፤
እኔ እንደምን ልሻገር፤
ተሻገሩት አሉ የሠሩት ምግባር፤
እኔ ባሪያሽ እንደም ልደር። 
ሰጊድ ሰላም! 
አንተ የአዳም ልጅ ተው አትርሳ፤
ነግ ትፈርሳለህ እንደጎታ፤
ጎታ ቢፈርስ ይደለዛል፤
የነፍስ ነገር የት ይደርሳል። 
ሰጊድ ሰላም! »
[ ሙሉ ግጥሙን ከድምጸ ተዋህዶ ራዲዮ ላይ ይስሙት]

እነዚህን በመሰሉ  በብዙ ስንኞች የተሞላውን ምለላዋን ስታቀርብ አፌን ከፍቼ እሰማ ነበር። ከቻልኩ  ግጥሙን እና ዜማውን ለመያዝ አብሬያትም እመልል ነበር። ከዚያም ሲነጋ ደግሞ ወደ እናት እና አባቴ ቤት ሄጀ ምለላውን ስጀምር አያቴ ትጠራኝ እና እባክህን አታንከልክላት ልጄ ትለኝ ነበር። እኔም አያቴ ሰማችኝ፣ አየችን እያልኩ ከእሷ እየተደበቅኩም ቢሆን ምለላዬን እለው ነበር። ለካስ አሁን ሲገባኝ አያቴ  አታንከልክላት እያለች ምለላዬን ትከለክለኝ የነበር የእርሷን ልመና ሌላው ሰው እንዳይሰማባት፣ ማለትም ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንባት ኖሯል። እኔ ይህንን መቼ አውቅኩና አያቴ! 

ብቻ ነሐሴ እስኪደርስ ጾመ ፍልሰታ እስኪገባ ድረስ የነበረኝ ጉጉት ልዩ ነበር። የአያቴን ምለላ ለመስማት። ታዲያ ምን ይሆናል «ሞትሰ ለመዋትኢ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ» ነውና ሞትም ለሁሉ የተገባ ነውና  አያቴም  በእለተ ሰኞ  በቅዱስ ገብርኤል  አመታዊ መታሰቢያ ቀን በወርሃ ሐምሌ በ1996 ዓ.ም. ወደማያልፈው ወደዘላለማዊው  ዓለም ተሸኜች። የምለላዋ ስንኞች ግን ዛሬም በልጅነት አእምሮዬ እንደተቀረጸው ከውስጤ አይጠፋም። ሁሌም ክረምት በገባ፣ ነሐሴ ሲብት ጀምሮ ፍልሰታ ስትመጣ አስባታለሁ፤ አስታውሳታለሁም።  ያኔ ሌት ተቀን ትለምነው የነበረው አምላክ ነፍሷን ከወዳጆቹ ቅዱሳን ጋር ይደምረው። 

ታዲያ ዛሬ ደግሞ ትዝታዬን የጫረብኝ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድምጸ ተዋሕዶ የሬዲዮ መርሐ ግብር በነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ዝግጅቱ ላይ «ምለላ» በሚል ርዕስ  የአያቴን የምለላ ግጥሞች ሲያቀርብ ነው። ግጥሞቹን ስሰማቸው ልክ ከአያቴ ጋር በሥጋ አንድ ላይ ሆኜ የሰማዋቸው እስኪመስለኝ ድረስ ውስጤን ሀሴት ሞላው። አያቴን ልክ ዘጠኝ ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሸ አሰብኳት። ይህ ነው እንግዲህ መሃላ አስፈርሶ ዛሬ ወደ ማኅበራዊ መገናኛዎች በተለይም ወደ ፌስ ቡክ ብቅ ያስባለኝ። እንዲህ አንዳንድ ትውስታ፣ ትዝታ ያላቸው አዳዲስ ነገሮች ተፈጥረው ተመልሼ እንገናኝ ድረስ ቸር ይግጠመን። 

ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡17
ሐይደልበርግ፣ ሀገረ ጀርመን

No comments:

Post a Comment