Saturday, August 11, 2012

ታዘብኳችሁ!



ወገኔ ምን ነካችሁ?
እንዲያው በብዙ ታዘብኳችሁ።
ፌስቡክን መሉ እንዳልነበር ጩኸታችሁ፤
ኢሜል ሙሉ እንዳለነበር ድጋፋችሁ፤
ብሉግ ሙሉ እንዳልነበር እልልታችሁ፤
ታዲያ ትናንት ምን ነካችሁ?
እንዲያው በብዙ ታዘብኳችሁ።
ሥዕል አድህኖ ስላያችሁ?
ደግሞም ምትሃት ነው ትላላችሁ፤
ለማን ነው ይሆን ድጋፋችሁ?
ለአትሌቶቹ ወይስ ለኢትዮጵያ ለሀገራችሁ ።
ለማን ይሆን ወርቁ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለመሰረት?
ለማን ይሆን ስሙ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለመሰረት?
አቋማችን አንድ ይሁን ለዓላማ ለአንድነት፤
ጹኑ አቋምም ይኑረን አንድ ኢትዮጵያዊነት።
ወርቁም ቢመጣ ለኢትዮጵያ ነው፤
ሥሟም ቢጠራ ኢትዮጵያ ነው፤
ታዲያ ወገኔ ሽሙጡ ምንድን ነው?
አዎ! መሰረትም ላቧ ጠብ ያለበት ደምወዟ ነው፤
ያም ሆነ ይህ ክብሩ ግን ለኢትዮጵያ ነው።
እናም ወገኔ አትሸወድ፤
አንዱም በአንዱ ላይ አይፍረድ፤
ድጋፋችን ከሰው ብቻ ወደ ኢትዮጵያም ይውረድ።
አዎ! ታምናለች፣ ያመነችበትንም ሰርታለች፤
ታዲያ መሰረት ምን አጠፋች?
ሥዕል አድህኖ ስላሳየች፤
ጣኦት አምላኪ ተባለች።
ግን ይህ አይደለም አምልኮ ጣኦት፤
ለቆሙበት አላማ ያመኑበትን መስራት፤
ደግሞም ከሁሉ በአምላክ እናት።
ታዲያ ለምን ነው ይህን ያክል ሽሙጡ፣
በውስጠ ወይራ ቃላትን ልውውጡ።
አዎ! አትሌቶቻችን ናቸው የእኛ ሞገስ የኛ አርዕያ፤
አዎ! አትሌቶቻችን ይገባቸዋል ክብር፣ ስለሆኑ ለኢትዮጵያ ማስጠሪያ፤
ድጋፋችን ግን ለሰው ሳይሆን ይሁን ለኢትዮጵያ።
ለአትሌቶቻችን እስኪ እንስጣቸው ሞራል፤
ክብር ለሚገባው ክብርም ቢሆን ይገባል።
ታዲያ ወገኔ ለምን አላደረግንም ይህን?
ፍቅራችንስ፣ ከአንገት በላይ ለምን ይሆን?
ፉጨታችን ለሰው ብቻ ለምን ይሆን?
ምን አመጣው  ሃሜትን?
ያየነው ባህሪ ከዘወትር ስለተለየብን፤
ወገኔ አትሳሳት ድጋፍክም ቢሆን፤
ለሀገር እንጂ ለሰው ብቻ አይሁን።
ታዲያ ወገኔ ምን ነካችሁ?
ፍቅራችሁንም ቀነሳችሁ?
እኔስ በብዙ ታዘብኳችሁ።
እንዲህ ነበር ወይ ወጉ፤
ላሸነፈ ሽልማቱ፣ ወርቅ ላመጣ ማዕረጉ፤
አቤት ባየን መለስ ብለን ከአባቶቻችን፤
ብናነብስ ብንጠይቅስ ምን እንደነበር ታሪካችን፤
ፍቅር እንጂ ማማት አልነበረም ባህላችን።
ተው ወገኔ ቆም ብለህ አስብ፤
ታሪክህንም ጠይቅ አንብብ፤
ከደመቀው አትዝፈን፤
እርስ በርስህ አትጨክን፤
ለኃጥአን የመጣው ለጻድቃን እንዳይሆን፤
ፍቅራችንም ከአንጀት እንጂ ከአንገት አይሁን።
እናም ወገኔ! እናስተውል፤
ዛሬ ብንተዛዘብ ቀንም ያልፋል፤
የጭንቅ ቀንም ይመጣል፤
ታዲያ ያኔ ምን ሊባል?
ጥሩነሽ ብቻ ትሩጥ አይባል፤
አይቀርም እኮ በመሰረት አደራ መጣል።
ስለዚህ ወገኔ ተጠንቀቅ፤
የምትናገረውን የምትጽፈውንም እወቅ፤
ከዚያም ይሆናል የተባረከ ወርቅ።
አለዚያ ግን ወገኔ፤
እንደታዘብኩህ እኔ፤
ጩኸት እንጂ የለምህም ወኔ።

ማስታወሻነቱ፦ ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል በቅ.ድንግል ማሪያምን ስዕለ አድህኖ ላይ እምነቷን በመግለጿ ሳያውቁ ሽሙጥን ላበዙባት ድል አድራጊዋ መሰረት ደፋር
አለምነው [ነሐሴ 5/2004 ዓ.ም.]








2 comments:

  1. Betam arif gitim new,keep it up alex.

    ReplyDelete
  2. thanx a lot!! i couldn't have said it better.betam betam betam amesegenalew.

    ReplyDelete