(ዓለምነው ሽፈራው)፦ ዛሬ ምሽት ከአንድ ሃበሻ ባለእንጀራዬ እና በአንድ ፍላት ውስጥ አብረውኝ ከሚኖሩ ጀመናዊ ወጣቶች ጋር አብረን እራት እየበላን ነበር። ምግቡን ተመግበን እንደጨረስን ገበታውን አነሳን። እነኝህ ወጣቶች በእድሜ እኩያቶቼ ቢሆኑ ነው። ለዚያም ይመስለኛል ተግባብተን ለማውራት አይከብደንም። ከዚያ ሃበሻው ወዳጄ እና አንዱ ጀርመናዊ ወጣት ከምን እንደተነሱ ባላስታውስም ስለትዳር ነክ ጉዳዮች ማውራት ጀመሩ። ከዚያ ያ ጀርመናዊው ወጣት በጀርመን ሀገር ብዙኃኑ ትዳር የሚመሰርተው (ተጋባን ብለው በማዘጋጃ ቤት የሚፈራረሙት ለማለት ነው) ዝቅተኛ ቀረጥ ለመክፈል ሲፈልግ ብቻ ነው አለን። ምንም እንኳን ይህንን ቃል ከዚህ በፊት ከሌላ ጀመርመናዊ ብሰማውም፣ ዛሬ ለምን ብዬ መጠየቅ ፈለግኩ። ፈልጌም አልቀረሁ ጠየቅኩት። በዚያው ጉንጭ ማልፋቱን አብሬ ተያያዝኩት። ምንም እንኳ አጥጋቢ አመክንዮ ባይኖረውም ያው «ግብቻን የሚመሰርቱት ዝቅተኛ ቀረጥ ለመክፈል ነው» ያለውን ያስረዳልኛል ያላቸውን ምክንያቶች ለመደርደር ተንደፋደፈ። ... ቀጠል አደረግን እና እሱ ስለ ጋብቻ ያለውን አስተሳሰብ ጠየቅነው። እሱም «እኔ የሴት ጓደኛ አለችኝ፣ በጣምም እወዳታለሁ፣ ነገር ግን ለትዳር ብዬ አስቢያት አላውቅም» አለ። «እርሷንስ ስለትዳር ጉዳይ አውርተሃት ታውቃለህን» ሲል ሃበሻው ጓደኛዬ ጠየቀው። ጀርመኔውም « አይ ሪልይ ኔቨር ቶክድ ኸር አቦውት ኢት፤ ኦኬ አይ ዊል ቶክ ኸር» አለን። በነገራችን ላይ ይህች ጀርመኔ የምትል ቃል የወሎን ሰው ወሎየ፣ የጎጃምን ሰው ጎጃሜ፤ የትግራይን ሰው ትግሬ፣ የጎንደርን ሰው ጎንደሬ ወ.ዘ.ተ. ካልክ የጀርመኑንም ሰው ጀርመኔ ማለት ይቻላል ሲል ኤፍሬም እሸቴ በአደደባይ ላይ አስፍሮት ነበር። ... ከዛም ይኼ ሃበሻ የሚለቅ ነው። ቀጠለ። «አንተስ ስለጋብቻ፣ ስለትዳር ምን ታስባለህ» ሲል ጠየቀው። ይኼ የፈረደበት ጀርመኔም «አይ ዶን ላይክ ጌቲንግ ሜሪድ ። አይ ጀስት ዋንት ቱ ኢንጆይ .... » አለ። ሁላችንም እየተቀባበልን «ትዳር ለአንተ ምንድን ነው? ለምንስ ማግባትን አልወደድክም?» በማለት በጥያቄ አጣደፍነው። ሲመልስም « ሲጀምር ትዳር መመስረት ነጻነትን ማጣት ነው። ሲቀጥል ትዳር ያለፈበት፣ በድሮ በአባቶቻችን ዘመን የቀረ ባህል ነው። እንዲያውም ትዳር መመስረት ዘመናዊነት አይደለም።» ብሎን እርፍ አለ።
እስኪ ያላችሁበት እና ያለፋችሁበት፣ እውነት ትዳር መመስረት ማለት ነጻነትን ማጣት ነውን? እውነት ትዳር ያለፈበት፣ ያረጀ፣ ያፈጀ ባህል ነውን? እንግዲህ በዚህ በጀርመኔው ሀገር ቢያንስ ለእሱ እንደዚህ መስሎ ታይቶታል። ወይም እንደህ እየተባለ እየተማረ አድጎም ሊሆን ይችላል። ለነገሩ አልፈርድበትም። አንድም ጀርመናዊ ወጣቱ ገና እንደእኔ አይነት ልጅ ነው እና የትዳርን ምንነት በደንብ አላሰበበት ይሆናል። አንድም በሙሉ ሀገሩ (ምዕራባዊያን በተለይም አውሮፓ) የቀደሙ አባቶቻቸውን ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል እና ወግ እየተው ሁሉንም እኛ በሰራነው እንሙት እያሉ ነው።
እሁን እኔን ያሳሰበኝ፣ ይህንንም ያክል ዙርያ ጥምጥም ያስኬደኝ አብሬው ስለበላሁት ሰው ለመተረክ አይደለም። ይህ ነገር ወደ ሃበሻ ምድር ኢትዮጵያ እየገባ አይደለም ወይ ለማለት ነው። አነጋገራችን፣ አመጋገባችን፣ አለባበሳችን፣ አካሄዳችን ብቻ ሁሉመናችን እንደ አባቶቻችን መሆኑን ትተን እንደ ምዕራባዊያን ለማድረግ ደፋ ቀና ስንል ያዬ በእውነት « እኔን ያዬ ይቀጣ» ያሰኛል ለአውሮፓዊያን። አሁን የአውሮፓ ማኅበረሰብ በተለይም አብዛኛው የወጣቱ ክፍል የአባቶቹን ትቶ በተለየ አለም ላይ መኖር የጀመረ ይመስለኛል። ለዚህ ብዙ ምስክሮች አሉ። እነሱን መዘርዘ አስፈላጊም አይመስለኝም። ብቻ እኛ ኢትዮጵያዊያንስ ወደየት እያመራን ነው? ወደምዕራባዊያን ወይም ወደቀደሙ አባቶቻችን .... ሁላችንም ራሳችንን ብንፈትሽ መልሱ ለሁላችንም ግልጽ ነው።
ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
ሃይደልበርግ፣ ጀርመን
ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
ሃይደልበርግ፣ ጀርመን
No comments:
Post a Comment