Thursday, October 31, 2013

እሱ እኮ ፈረንጅ ነው

        (ዓለምነው ሽፈራው፡ ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ) ፡ መዛግብት የሚያስረዱን  ቅኝ ግዛትን  በ19ኛ እና በ20ኛ መቶ ክፍለ ዘመን እንደነበረ ነው። ብዙ የአፍሪካ ሃገራት በምዕራባዊያን በተለይም በአውፓዊያን ቅኝ ግዛት ውስጥ ወድቀውም ነበር። ምንም እንኳን ሀገራቱ ነጻነታችውን ያገኙ ቢሆንም ቅሉ በአስተሳሰብ ግን ዛሬውንም ከቅኝ ግዛት የወጡ አይደሉም። ይህን እጣ ፈንታ ሳይደርሳቸው ከቀሩት  ሁለት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንደኛዋ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት መላለቀቅ አርእያ የሆነች አንዲት ሀገር ነበረች። የብዙ ሀገራት ጀግኞች  እርሷን አይነተው ስለነጻነታቸው ታግለዋል። ታግለውም አልቀሩም ነጻነታቸውን መጎናጸፍንም ችለዋል።  ይህችም ሀገር ኢትዮጵያ ነች። 
ኢትዮጵያ ቆራጥ የሆኑ ጀግና ሃይማኖተኛ ልጆች ስለነበሯት ቅኝ ገዥ ነን ብለው የዘመቱትን አውሮፓዊያንን አንበርክካ የመለሰች ነበረች። ልጆቿም ነጻነቷን ሲጠብቁ እንደቅኝ ገዢዎች በዘመናዊ መሳሪያ ሳይሆን፣ በሀገር በቀል መሳሪያዎች ግፋ ቢልም በቆመህ ጠብቀኝ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው። እነዚህ ጀግና ልጆቿም እናሰልጥናችሁ ሲላቸው እንደሚያሰየጥኗቸው አውቀው፤ አላፊ የሆነውን የነጭ ገንዘብ ሳያታልላቸው፣ ስለማንነታቸው ሲሉ ታግለዋል፣ ተፋልመዋል፣ አንበርክከውማል። የታሪክ ጸሐፊም አይደለሁም፣ የተነገረን ታሪክም ለመድገምም አይደለም።  ነገር ግን  ይህንን ላነሳ የወደድኩት  ዛሬ ላይ የእኔ ዘመን ትውልድ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው በቅኝ ግዛት ሥር መሆኑን ሳስበው ስለሚቆጨኝ፣ ምናልባት ሰሚ ካለ ልብ ቢል ብየ ነው። ይህንንም የ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ቅኝ ግዛት ብየዋለሁ። ነገሩ እንዲህ ነው። 
ያች ለአውሮፓዊያን ኃያላን ቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች ሀገር፣ ያ ለጣሊያን ያልተንበረከከ ጀግና ህዝብ ዛሬ እንኩላችሁ ብሎ እጁን እየሰጠ እንደሆነ ይሰማኛል። እንዴት የሚል አይጠፋም። 
ነጪና ሃበሻ (ጥቁር ኢትዮጵያዊ  ህዝብ)  የተለያዩ ፍጥረታት ይመስል፤ ነጪ ማለት ከጥቁር በላይ ነው ብሎ የሚያስብ ብዙ ሰው እንዳለ ለማየት በሀገራችን ያሉ አንዳንድ ተቋማት ውስጥ ብቻ የሚሰራውን ማየት ከበቂ በላይ ነው። ለምሳሌ ያክል፡-
  1. አንድ ሃበሻ እና ነጪ በአንድ ላይ ወደ አንድ መስሪያ ቤት ቢሄዱ ቅድሚ ለማን እንደሚሰጥ ሁሉም ያውቀዋል። «ቅድሚ ለነጭ» የሚል ህግ ማን እንዳወጣ ባላውቅም፣ «ቅድሚያ ለሴቶች» እንደሚባለው ቅድሚያ ለነጮች ነው። ለምን ስትሉም «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጅ ነው» ነው መልሱ።  
  2. ወደ አንድ ፍተሻ ወደ አለበት ቦታ አንድ ሃበሻና አንድ ጪ አብረው ቢገቡ፣ መከረኛው ሃበሻ የለበሰው እስኪቀደድ ድረስ ታሽቶ ይፈተሻል። ነጩ የሆነ እንደሆነ  አይደለም ፍተሻ ቀና እንኳን ብሎ ማን ነህ የሚለው የለም።   ለምን እኔ ብቻ እፈተሻለሁ  ስትሉም «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጅ ነው» ነው መልሱ።  
  3. ሃበሾች በሚዝናኑባቸው ሆቴሎች እና ፊልም ቤቶች በአጋጣሚ አንድ ነጭ ቢመጣና ወይ መቀመጫ ቦታ ቢጠፋ ወይም ያለው ለነጩ ባይጥመው የሆቴሉ ወይም የፊልም ቤቱ አስተናጋጆች በሙሉ በሃበሻው ላይ አሲረው እንደሚያስነሱትም በአይኑ ካየ ሰምቻለሁ። ለምን ብሎ ቢጠይቅም  «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጅ ነው» ነው መልሱ።
  4. ጎበዝ እና ታታረ  ሃበሻ የሚሰራው አጥቶ እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ፤ የእስያን ነጪ ማጋሰሥ ምን ይሉታል። ይህንን ለማየት በየዩኒቨርሲቲዎቻችን የተሰገሰጉ «መምህር» ነን ባይ ህንዳዊያንን  (ጊዜ ቢፈቅድ ብዙ እንመለስበታለን)፤ በየታላላቅ የሃገር ሃብት የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እንደ ጉንዳን የሚትመለመሉ  «መሃንዲስ» ነን ባይ ቻይናዊያንን ማየት ከበቂም በላይ አሰልች ነው። መከረኛው ሃበሻ ከአሥራ አምስት አመት በላይ ለፍቶ፣ ተንጠግሮ፣ የሀገር ሃብትን አባክኖ  ተምሮ ቢያገኝ አንዲት ለእለት እንጀራ የማትበቃ ደምዎዝ የሚያስከፍልን  ሥራ፤ ካልሆነ ደግሞ ኮብል ስቶን ጠራቢነት፣ ሲብስም ጎዳና ተዳዳሪነት የሚፈረድበት ለምን ይሆን? እውነት እውቀቱ ከህንዳዊያን እና ከቻይናዊያን የሃበሻው አንሶ ነውን?  ህንዳዊያን እና ቻይናዊያንስ ልሂቃን ስለሆኑ ነው? እኔ ግን እላለሁ፤ መመካትም አይደለም ከ«ዶከተር» ነኝ ባይ ህንዳዊ ምንም ፊደል ያልቆጠሩት ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ሃበሾች ያስተምሩኝ። በ«ኢንጅነር» ነኝ ባዩ ቻይናዊ ከሚሰራ ይልቅ ሃበሻ የሰራው ይግደለኝ።  ለምን እንዲህ ይሆናል ብሎ ለሚጠይቅም  «እንዴ እነሱ እኮ ፈረንጅ ናቸው» ነው መልሱ።
  5. ነጪ ያደረገው ሁሉ ትክክል ነው ብሎ አሳቢ ሃበሻም አይጠፋም። ያንንም አደርጋለሁ በማለት ሌት ከቀን በማሰብ ብቻ ጊዜው የሚያጠፋ ብዙ አለ። ለምሳሌ በአነጋግገሩ፣ በአለባበሱ፣ በአካሄዱ ወ.ዘ.ተ. ነጪ መምሰል ብቻ ህልሙ የሆነ። ህልሙ ሁሉ የነጪን ሥራ። ነጪ ገደል ቢገባ እና ተከተለኝ ቢለው የሚከተለውም አይጠፋም ይመስለኛል።  ለምን ቢሉ «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጂ ነው » የሚል ይመስለኛል። 
እንግዲህ ይህኔ ነው ነጪ በሃበሻ ላይ በሀገሬም አንደኛ ዜጋ፣ በሀገርህም አንደኛ ዜጋ፤ አንተ ግን በሀገርህም በሰውም ሀገር ሁለተኛ ዜጋ  እያለ የሃበሻውን ሞራል የሚያንቋሽሽ። ታዲያ ይህ ቅኝ ግዛት መባል ይነሰው? ለዚህ ቅኝ ግዛትስ ማን ይሆን ተጠያቂው? ነጩ ወይስ ሃበሻው? እንደኔ ሃበሻ እራሱ ና ብሉ ጎትቶ ያመጣው ነው ባይ ነኝ። 
ይህንን ትህትና ነው እንበለውን? እንግዳ አክባሪነት ነው እንበለውን? ምን እንበለው። ትህትና እማ ቢሆን አንተ ነጪ አንተ ጥቁር ነህ፤ አንተ ከአውሮፓ፣ ከአማሪካ፣  ከእስያ፣ ከአፍሪካ እንተ ደግሞ  ከኢትዮጵያ ነህ ብሎ መከፋፈሉ ባልነበረ። አዛውንት ተቀምጦም ወጠምሻ ነጪ ቅድሚያ ባልተሰጠው ነበረ። እንግዳ አክባሪነት እንዳልለው እነዚህ ነጮች እስከ መቸ ነው እንግድነታቸው? እንግዳስ (ለጊዜውም ቢሆን ነጪን እንግዳ ብየዋለሁ) ታማኝ፣ ሃበሻ ደግሞ አጭበርባሪ የሆነው መቼ ነው? እንግዳ ሊያጭበረብር አይችልም ያለውስ ማን ነው? ... ብቻ አንዱም ምክንያት ሊሆንልኝ አልቻለም። ለእኔ ግን የዚህ ሁሉ በሃበሻ ላይ በደል ለትህትናም ለእንግዳ አካባሪነትም ሳይሆን «ያለጦርነት የመጣ ቅኝ ግዛት» ነው። 
እኔ ሁለት የነጪ ሀገራትን እንዴት አንድን ሰው እንደሚያስተናግዱ «በመጠኑም» ቢሆን አይቻለሁ። አንዱም ሀገር ላይ አንተ የሀገሪቷ ዜጋ ሥለሆንክ ወደኋላ ቆይ፣ አንተ ደግሞ እንግዳ ስለሆንክ ቀድመህ ትስተናገዳለህ ሲል አላየሁም። ሁሉንም እኩል ለማድረግ ሲጥሩ አይቻለሁ። እውነት ነው የሃገራቸው ዜጋ ተቀምጦ ለሌላ ሀገር ዜጋ ሥራም ሲሰጡ አላየሁም። ከእነሱ የተረፈውን ለሌላው ግን ከመስጠትም ወደ ኋላ ሲሉም አላየሁም።  እኔ ይህንን የሚያደርጉት የሌላውን ዜጋ ለማክበር ብለው ሳይሆን፤ ህጋቸው በራሱ ሁሉንም ሰው በእኩል እንዲያከብር ስለሚያዝዛቸው እና ህግጋቶቻቸውን ጠንቅቀው ስለሚያከብሩ ነው። እኛ የዛሬ ሃብሾች ግን «ወይ ራሳችንን አላስከበርን፤ ወይ እንደነጭች ህግጋቶቻችን አክብረን ሁሉንም ሰው በእኩልነት አላየን»።  ዝም ብለን ሁል ጊዜ «እሱ እኮ ፈርንጅ ነው» እያልን በራሳችን ላይ ጉድጓድ ስንቆፍር እንውላለን።

ለዚህ መፍትሔውስ ምን ይሆን? (ለውይይት ክፍት ነው፤ ሐሳብ እንስጥበት።)

ሐይደልበርግ፣ ጀርመን 





















(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Wednesday, October 23, 2013

የለውጥ ጅማሮ

        (ዓለምነው ሽፈራው፡ ጥቅምንት 14 ቀን 2006 ዓ.ም.) ፦ ለውጥ የተጀመረ ይመስለኛል።  ላለፉት ጥቂት አመታት ወርኃ ጥቅምት እና ሚያዚያ ወይም ግንቦት ሲደርስ አንዳንድ የሁሉንም ክርስቲያን ቀልብ የሚስቡ፣ የሚያስደስቱ፣ ከዚያ በተቃራኒው  የሚያናድዱ ነገሮች መስማት የተለመደ ነበር።   ነገሩ እንዲህ ነው።
የስዕል ምንጭ፡ ማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር 
በኢ.ት.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የቤተክርስቲያኗ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደርጋቸው ሁሉት አመታትዊ   ጉባኤያት የሚካሄዱት በነዚህ ወቅቶች ነው።  እነዚህ ጉባኤያት ቤተክርሲቲያኗን የተመለከቱ መንፈስዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባቸው ናቸው።  ውሳኔዎቹም ይግባኝ የሌላቸው ናቸው። ምክንያቱም የሚወስናቸው የቤተክርስቲይኗ የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነውና።   ልክ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥቅምት እና ሚያዚያ ወይም ግንቦት ላይ ጉባኤውን  ሲጀምር እውነተኛውም ሐሰተኛውም መረጃ እንዳደርሳለን ባይ ጡመራ በሙሉ ስራውን አጧጡፎ ይጀምራል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በጸሎት ጉባኤውን ሲከፍት፣ በጸሎት ከፈተ፤ አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ ሲሰይም፣ አጀንዳ  አርቃቂ ኮሚቴ አቋቋመ፤ አንጀንዳዎች ሲለዩ፣ እነዚህ አጀንዳዎችን መርጧል፣ እነዚህን አልመረጠም፤ ወ.ዘ.ት. በማለት ይጀምራሉ። ከዚያም ገና የጉባኤው የመጀመሪያ እለት ላይ ብጹዕ አቡነ እገሌ እንዲህ ብለው፣ ብጹዕ አቡነ እገሌ እንዲህ ብለው አቡነ እገሌ ገስጿቸው፤ ብጹዕ አቡነ እገሌ እንዲህ አርድገው እንዲህ ተባሉ  ወ.ዘ.ተ.... በማለት ይቀጥላሉ። እንዲህ እያሉ የሲኖዶሱን ስብሰባ በሙሉ እውነቱንም ወሸቱንም፣ የተባለውንም ያለተባለውንም ሲያጎርፉት ጦማሪዎች አብረው ከሲኖዶሱ ጋር አብረው የሚሰበሰቡ ይመስል ነበር። ይህንን ተከትሎ የህዝበ ክርስቲያኑ ልብም አብሮ ከወዲያ ወዲህ ሲል ሲብከነከን ይሰነብታል።   አይ ለምን አባ እገሌ እንዲህ አሉ? አባ እገሌስ እንዲህ ያሉት ለንምድን ነው? እንዲህ ማለት ነበረባቸው፤ ኤጭ እሳቸውማ ልማዳቸው ነው፤ እንዲህ ብለው መናገር ነበረባቸው፣ ሲኖዶሱ እንዲህ ብሎ መወሰን ነበረበት፣ ወ.ዘ.ተ. በማለት  እነዚህ መከረኛ አባቶች በክፉም በደጉም ሲቦጭቃቸው ይውላል ያድራል። ሥራው ሁሉ ስለሲኖዶሱ ጉባኤ ማሰብ ብቻ ይሆናል።  «ሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማኀበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ አንተ ግን ሥራህን ሥራ!» እንዳሉት ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ፤ ሥራ መስራቱን ትቶ ሁሉም ስለ  ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሎ ወሬ ለቀማ ሲጣደፍ ይስተዋል ነበር። ሥራውን መሥራት ትቶ ጉዳዩ የሚያገባው ቢሆንም ሲኖዶሱ ውስጥ ገብቶ መወሰን የማይችለውን፤ ጉዳዩ የሚመለከተው ቢሆንም ገብቼ አንድ የሲኖዶ አባል ተሰብሳቢ ልሁን ብሎ ማመልከቻ ማስገባት የማይችለውን፣ እንዲሁ በሚያገባውም፣ በማያገባውም፣ በሚመለከተውም፣ በማይመለከተውም የራሱንም አዕምሮ  ሲያስጨንቅ እድሜውን ይገፋል። ከነዚህ ውስጥ እኔም አንዱ ሰለባ ነበርኩ። የእሱ ሃሳብ አባ እገሌ ተናገሩት፣ ወይም  ሲኖዶሱ  የሱን ሃሳብ የሚቀርብ ወሰነ ሲባል ደስ የሚለው፤ የእሱን ተቃራኒ አባ እገሌ ተናገሩ ሲባል በእኒያ አባት ላይ የሚያጉረመርም፤ የእሱን ሃሳብ  የመሰለ ሃሳብ በሲኖዶሱ ጉባኤ ውስጥ ተነስቶ ተቀባይነት አጣ ሲባል ሲኖዶሱ መንፈስ ቅዱስ ርቆታል እስከ ማለት የሚደርስም ብዙ ነው። ወ.ዘ.ተ.

መረጃ በጊዜው ለሚመለከተው አይድረስ አልልም። መድረስም አለበት። ሰውም መረጃን መፈለጉ ክፉት የለውም፤ ነገር ግን መረጃው ለምን፣ ከማን፣ እንዴት እና መቼ የሚሉት ጉዳዮች ወሳኝነት አላቸው። የቤተክርስቲያኗን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በተለይም ወሳኝ የሆነውን የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ  መረጃ ግን ቤተ ክርስቲያኗ በኦፊሲያል  እንደየ አስፈላጊነቱ (ለህዝበ ክርስቲያኑ መነገር የሚገባውን) ማድረስ ግዴታዋም ነው፤ ኃላፊነትም አለባት። ይሁን እንጂ  እውነት ይሁን ሐሰት ማጠራት እንኳን በማይቻልበት፤ ማን እንደሚጽፈው በማይታውቅበት፤ የመረጃው ምንጭ ከየት እንደሆነ ሳይታወቅ የቤተ ክህነት ምንጮቻችን እንደነገሩን እየተባለ በድብቅ በሚጻፍበት ዘመን  መረጃውን ቀድመን  በስማ በለው ከሚሰሙት ጦማሪዎች  መስማት የለበትም።  ህዝቡም በመረጃ ሲጭበብረበር፣ ሲምታት ዘመኑን ሙሉ መኖር የለበትም።  የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ወቅቱ በሚፈቅደው ሁሉ መረጃውን ለልጆቿ ብታደርስ፤ ጳጳሳቱም አይሰደቡም፣ ቤተ ክህነቱም አይነቀፍም ነበር። እንደአለመታደል ሆኖ እስከአሁን ይኼንን ሲሰራበት አላየንም። ዛሬ ግን ለውጥ የተጀመረ ይመስለኛል።

እንደተለመደው ሁሉ የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከተጀመረ ሁለት ቀናት አስቆጥሯል። በመጀመሪያው እለትም የጉባኤውን መጀመር አስመልክቶ  ቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ማንነታቸው የሚታወቁ የዜና ምንጮችም ሆነ በድብቅ የሚጽፉ ጦማሪዎች መረጃውን አድርሰውናል። በቤተክርስቲያኗም ድረ ገጽ ላይ መረጃው ለሁሉም በይፋ ተለጥፏል።  ይህ በጣም አስፈላጊና ተገቢ ነው። ይበልም ያስብላል። ከዚህ ያለፈ መረጃ እስከ አሁን አላየሁም።  የለውጥ ጅማሮው አንድ እርምጃ ይኼ ነው።

ሌላኛው ከዚህ በፊት የሚደረጉትን ጉባኤያት መረጃ አንድ በአንድ እውነትም ይሁን ሐሰት ሳይጣራ፤ ውሳኔ ይሁን ሀሳብ ሳይታወቅ፤ አንዱ ሊቀ ጳጳስ ያነሱትን ሃሳብ የቅዱስ ሲኖዶዱ ውሳኔ ይሁን የሊቀ ጳጳሱ የግል ሃሳብ ሳይለይ እንዲሁ  በጅምላ የጠዋቱን ከሰዓት፣ የከሰዓቱን ውሎ በአመሻሽ እንዲሁ እንደወረደ ይበትኑት ነበር። መረጃው ከየት፣ በየት፣ እንዴት፣ መቼ፣ ለምን እንደወጣ እንኳን ምንም አይነት ማስረገጫ የለም። ብቻ ጦማር ላይ ይከተባል፣ አድሜም ያነባል፣ እንደፈለገው ይተረጉማል፣ የፈለገውንም ያደርግ ነበር። በዚህ ላይ ሁሉት ነገሮች ይታዩኛል። አንድ ጦማሪያኑ ይህንን ያልተሟላ፣ ያልተጣራ መረጃ ከየት ነው የሚያገኙት? ጦማሮያኑ የሲኖዶሱ አባላት ናቸውን ያስብላል። ወይንስ የሲኖዶሱ አባላት ወደ ስብሰባው ሲገቡ ስልካቸውን ከፍተው ከጦማሪያኑ ጋር ሲነጋገሩ ነው የሚውሉት? ወይንስ ጦማሪያኑ የሲኖዶሱ አባላት የሚያስቡትን እና የሚናገሩት የመገመት፣ የመተንበይ ሃብተ ትንቢት ተሰጥቷቸዋል?  ወይንስ ቤተ ክርስቲያኗ ለድብቅ ጦማሪዎች ብቻ መረጃውን በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው፣ በየቅጽበቱ ታደርስ ነበር? በእርግጠኝነት የመጨረሻውን  ቤተ ክርስቲያኗ አታደርግም። እንዲደረግም አትፈቅድም።  ታዲያ የመረጃው ምንጭ ከየት ነበር? መልሱን ለጦማርያኑ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ትቸዋለሁ።  ሁለት የቤተክርስቲያኗ አስተዳደር ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለምዕመኑ በጊዜው የማያደርስበት ምክንያቱስ ምን ነበር? የማስተላለፊያ አቅም ጠፍቶ? ዘመኑ መረጃ ለማዳረስ ከባድ ሆኖ? ወይስ መረጃው ለምዕመናኑ መድረሱ የማያስፈልግ ሆኖ ነውን? ወይስ ያልታወቀ ምክንያት ነበር? መልሱን ከእኔ ይመስለኛል ግምት ይልቅ  ከቤተክህነቱ እና ከሲኖዶሱ አባላት መስማት ይሻላል።

በአሁኑ ጉባኤ  ግን ይኼው አርባ ስምንት ሰዓት አለፈ አንድም ስለሲኖዶሱ ስብሰባ መጀመሩን ከማብሰር  ውጭ የተባለም፣ የተነገረም፣ የተጻፈም ነገር አላየሁም፤ የለም።  ለዚህስ ምክንያቱ ምን ይሆን?  ጥቂቶቹ ግሞቶች እነዚህ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ስለውሏቸው በየሰዓቱ ለጦማርያን መረጃ ከመስጠት ይልቅ ወደ ጉባኤያቸው ያተኮሩ ይመስለኛል። የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የውሉ ዘገባ የሚጻፍለት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ውሳኔ የሚወሰንበት ነውና። አንድም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ አንገብጋቢ የሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች የሉም ብሎ በማሰብ ጦማርያኑ ከቤተ ክህነቱ ራቅ ብለው ይሆን? ይህ ነው እንዳይባል በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ውስጥ በአስቸኳይ መፈታት የሚያስፈልጋቸው አያሌ የሆኑ አንገብጋቢ ውስጣዊ እና ውጫው ጉዳዮች አሉ። እነዚህን አይደለም አይን ያለው፣ አይነ ስውርም ያያቸዋል፤ አይደለም ጆሮ ያለው፣ ደንቆሮም ይሰማቸዋል።  አንድም ቤተክርስቲያኗ የግባኤዬን መረጃ እንደፈለጋችሁ እየቆነጻጸላችሁ፤  «መጣሁልሽ» እያለች ጩኸት እንድምታበዛ ቀበሮ በጎቼን አታስጨንቁ፤ እነሱም ሥራቸውን ይስሩበት፤ እናንተም ስራችሁን ፈልጉ፤ ብላ መረጃው ከጉባኤው እንዳይወጣ ወስና ይሆን። እነውነት ነው የቤተክርስቲያንን መረጃ ቤተክርስቲያን ስታውጀው እንጂ በስማ በለው ሲሰማ ለጆሮ አይጥምም። አንድም ጦማርያኑ የሚጦምሩበት በይነ መረብ አገልግሎቱን አቁሞ ይሆን? እዲህ እንዳንል ብዙዎቹ የሚጠቀሙበትን ይኼው እኔ አሁን ይህንን ጽሑፍ እየከተብኩበት ነው።   አንድም የሲኖዶሱ ስብሰባ በአንድ ቀን ተፈጽሞ ይችል ይሆንን። ይህ ቢሆንም ቢያንስ መፈጸሙ ሳንሰማ አንቀርም ነበር። ታዲያ ለምን ይሆን ስለሲኖዶስ ስብሰባ አንድም ሳንሰማ አርባ ስምንት ሰዓት የሞላው? እንደ እኔ የለውጡ አንዱ እርምጃ  ነው ባይ ነኝ። የቤተ ክህነቱ አስተዳደር ለምን መረጃውን በጊዜው አላደረሰንም የሚል ሃሳብ ይነሳ ይሆናል። ያደርሰናል ብለን እንጠብቅ። እንዲያው በየቀኑ የተባለውን ሁሉ የሚናገር ከሆነማ ምኑን ከድብቅ ጦማሪያን ተሻለ? ሃሳቡስ መቸ ተነስቶ፣ መቼ ምልዓተ ጉባኤው ተወያይቶበት ውሳኔ ሰጠበት ይበለን? «ከረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል» እንደሚባለው ረጋ ብሎ መረጃውን ሊያደርሰን ይገባል። ቤተ ክህነቱ ይህንን እንደሚያደርግም ተስፋ አለኝ። ለውጡም እንደሚቀጥል ተስፋዬ ሙሉ ነው።

ባለፈው አመት የካቶሊካዊያን ቤተክርስቲያን ፖፕ (እንደ ፓትርያርክ ማለት ነው) ስልጣን በቃኝ፣ ኃላፊነት በዛብኝ ብለው ስልጣናቸው ለሰጣቸው የቤተክርስቲያናቸው አስተዳደር በአጭር ጊዜ ውስጥ አስረክበዋል። ምንም እንኳ በእምነት ባይመስሉንም አስተዳደራቸውን እንደምሳሌ ብንወስደው አይከፋም።  «የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች» እንዳትሉኝ። «መልክ ስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ» አይደል ብሂሉ። ቅድስት ተዋህዶ  እምነታችንን ይዘን አስተዳደርን ከጎረቤት ብንማር ክፋት የለውም ነበር።
የቤተክርቲያኒቱ አስተዳደርም ተተኪውን ፖፕ ለመምረጥ ሲዘጋጅ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሳለፈው በኋላ የምርጫው እለትም ደረሰ። የምርጫው ሂደት በእጅጉ  የሚያስቀና፣ የእምነቱን ተከታይም የሚያጓጓ፣ የሚያኮራም ነበር። የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንንም ቀልብ የገዛ ነበር። ምርጫው የተደረገባትን የቫቲካን ግዛት፣ የሮምን ከተማም ማን ይሆን በሚል ጉጉት ያስጨነቀም ነበር። ምርጫው በሚደረግበት ወቅት መራጮች ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ  ከማንም ሰው ጋር አልተናኙም። በነገራችን ላይ በካቶሊክ ቤተከርስቲያ የፖፕ መራጮች እና ተመራጮች  ካርዲናሎች ማለትም ጳጳሳት ብቻ ናቸው። ከውጭው ህዝብ ማለትም ከእምነቱ ተከታዮች እና ከመገናኛ ብዙኃኑ ማኅበረሰብ ጋር የሚገናኙት እና የሚግባቡት  በ«ጭስ» ምልክት ብቻ  ነበር። ፖፑ ሲመረጥ የጭሱን መልክ የተለየ በማድረግ መመረጡን ያበስራሉ። ፖፑ በአንድ ቀን ባይመረጥ ለብዙ ቀናት ይህ ሁኔታ ይቀጥላል። ፖፑ እስከመረጥ ድረስ ማለት ነው።  ከዚያ በኋላም  መራጮች ከውጪው ማኀበረሰብ ጋር መገናኜት ይችላሉ። መራጮችም መገናኛ ብዚኃንም የፈለጉትንም መናገር ይጀምራሉ። እስከዚህ ሰዓት ድረስ ግን ማን እንደሚመረጥ፣ ማን እጩ እንደሆነም ማወቅ በፍጹም አይቻልም።

የካቶሊካዊያኑን  አስተዳደር ማንሳት የፈለግኩበት እና በእኛ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ መሆን ያለበት አንድ ጉዳይ  አለ። ያም የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጉባኤ ሲጀመሩ ጉባኤው እስኪፈጸም ድረስ ከምዕመናን እና ከውጭው ማኅበረሰብ  ከመገናኛ ብዙኃን  ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ ቢቻልም ፈጽሞውኑ ማስቀረት ነው። ሲኖዶስ ስብሰባ ተሰብስቦ የዋለን አንድ የሲኖዶስ አባል ከስብሰባ ሲወጣ መረጃ ስጠን ብሎ በማጣደፍ፣ የሲኖዶሱን አካሄድ በመገምገም የዚያንንም የሲኖዶስ አባል ሃሳብ መቀልበስ እና በቀላሉ መለወጥ ይቻላል። ምክንያቱን የሲኖዶሱ አባላት ጳጳሳት ቢሆኑም እንኳ ሰው ናቸው እና ሊሳሳቱ፣ ሊታለሉ ይችላሉ። ለዚህ ዋነኛው  መፍትሄ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ወቅት  የሲኖዶሱን አባላት  ከሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ ነው። ለመገናኛ ብዙኃን ወይንም ለምዕመናን መረጃ ለማድረስም ራሱ ሲኖዶሱ የሚመልከተውን አካል ወይንም የሲኖዶስ አባል ሊሰይም እና መረጃ እንዲያደርስ ቢያደርግም መልካም ነው።  ይህ ከሆነ የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ወጤታማ፣ ውሳኔውም ርቱእ ይሆናል። ካህናቱና ምዕመናንም ውሳኔውን አሜን ብሎ በመቀበል ለተግባራዊነቱ ይጥራሉ።

እግዚአብሔር አምላክ ለአባቶቻችን ስለቤተ ክርስቲያን መልካም ነገር የሚወያዩበት፣ የሚወስኑበትን አቅሙን፣ ጸጋውን ያድልልን። የአባቶቻችን በረከት ይደርብን።  አሜን።

ቤተክህነታችን ሆይ ትንሳኤህን ያሳየን!!!
ሃይደልበርግ፣ ጀርመን!


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Monday, October 21, 2013

ጀርመናዊው ወጣት!


     (ዓለምነው ሽፈራው)፦ ዛሬ ምሽት ከአንድ ሃበሻ ባለእንጀራዬ  እና በአንድ ፍላት ውስጥ አብረውኝ ከሚኖሩ ጀመናዊ ወጣቶች ጋር አብረን እራት እየበላን ነበር።  ምግቡን ተመግበን እንደጨረስን ገበታውን አነሳን። እነኝህ ወጣቶች በእድሜ እኩያቶቼ ቢሆኑ ነው። ለዚያም ይመስለኛል ተግባብተን ለማውራት አይከብደንም።  ከዚያ ሃበሻው ወዳጄ እና አንዱ ጀርመናዊ ወጣት ከምን እንደተነሱ ባላስታውስም ስለትዳር ነክ ጉዳዮች  ማውራት ጀመሩ። ከዚያ ያ ጀርመናዊው ወጣት በጀርመን ሀገር ብዙኃኑ ትዳር የሚመሰርተው (ተጋባን ብለው በማዘጋጃ ቤት የሚፈራረሙት ለማለት ነው) ዝቅተኛ ቀረጥ ለመክፈል ሲፈልግ ብቻ ነው አለን። ምንም እንኳን ይህንን ቃል ከዚህ በፊት ከሌላ ጀመርመናዊ ብሰማውም፣ ዛሬ  ለምን ብዬ መጠየቅ ፈለግኩ። ፈልጌም አልቀረሁ ጠየቅኩት። በዚያው ጉንጭ ማልፋቱን አብሬ ተያያዝኩት። ምንም እንኳ አጥጋቢ አመክንዮ ባይኖረውም ያው «ግብቻን የሚመሰርቱት ዝቅተኛ ቀረጥ ለመክፈል ነው»  ያለውን ያስረዳልኛል ያላቸውን ምክንያቶች ለመደርደር ተንደፋደፈ። ... ቀጠል  አደረግን እና እሱ ስለ ጋብቻ ያለውን አስተሳሰብ ጠየቅነው። እሱም  «እኔ የሴት ጓደኛ አለችኝ፣ በጣምም እወዳታለሁ፣ ነገር ግን ለትዳር ብዬ አስቢያት አላውቅም» አለ። «እርሷንስ ስለትዳር ጉዳይ አውርተሃት ታውቃለህን» ሲል ሃበሻው ጓደኛዬ ጠየቀው። ጀርመኔውም « አይ ሪልይ ኔቨር ቶክድ ኸር አቦውት ኢት፤ ኦኬ አይ ዊል ቶክ ኸር» አለን። በነገራችን ላይ ይህች ጀርመኔ የምትል ቃል የወሎን ሰው ወሎየ፣ የጎጃምን ሰው ጎጃሜ፤ የትግራይን ሰው ትግሬ፣ የጎንደርን ሰው ጎንደሬ ወ.ዘ.ተ. ካልክ የጀርመኑንም ሰው ጀርመኔ ማለት ይቻላል ሲል ኤፍሬም እሸቴ  በአደደባይ  ላይ አስፍሮት ነበር።  ... ከዛም ይኼ ሃበሻ የሚለቅ ነው። ቀጠለ። «አንተስ ስለጋብቻ፣ ስለትዳር ምን ታስባለህ» ሲል ጠየቀው። ይኼ የፈረደበት ጀርመኔም «አይ ዶን ላይክ ጌቲንግ ሜሪድ ። አይ ጀስት ዋንት ቱ ኢንጆይ .... » አለ። ሁላችንም እየተቀባበልን «ትዳር ለአንተ ምንድን ነው? ለምንስ  ማግባትን አልወደድክም?» በማለት በጥያቄ አጣደፍነው። ሲመልስም  « ሲጀምር  ትዳር መመስረት ነጻነትን ማጣት ነው። ሲቀጥል  ትዳር ያለፈበት፣ በድሮ በአባቶቻችን ዘመን የቀረ ባህል ነው። እንዲያውም  ትዳር መመስረት ዘመናዊነት አይደለም።» ብሎን እርፍ አለ። 
እስኪ ያላችሁበት እና ያለፋችሁበት፣ እውነት ትዳር መመስረት ማለት ነጻነትን ማጣት ነውን? እውነት ትዳር ያለፈበት፣ ያረጀ፣ ያፈጀ ባህል ነውን? እንግዲህ በዚህ በጀርመኔው ሀገር ቢያንስ ለእሱ እንደዚህ መስሎ ታይቶታል። ወይም እንደህ እየተባለ እየተማረ አድጎም ሊሆን ይችላል።  ለነገሩ አልፈርድበትም። አንድም ጀርመናዊ ወጣቱ ገና እንደእኔ አይነት ልጅ ነው እና የትዳርን ምንነት በደንብ አላሰበበት ይሆናል። አንድም በሙሉ ሀገሩ (ምዕራባዊያን በተለይም አውሮፓ) የቀደሙ አባቶቻቸውን ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል እና ወግ እየተው ሁሉንም እኛ በሰራነው እንሙት እያሉ ነው። 
እሁን እኔን ያሳሰበኝ፣ ይህንንም ያክል ዙርያ ጥምጥም ያስኬደኝ አብሬው ስለበላሁት ሰው ለመተረክ አይደለም።   ይህ ነገር ወደ ሃበሻ ምድር ኢትዮጵያ እየገባ አይደለም ወይ ለማለት ነው። አነጋገራችን፣ አመጋገባችን፣ አለባበሳችን፣ አካሄዳችን ብቻ ሁሉመናችን እንደ አባቶቻችን መሆኑን ትተን እንደ ምዕራባዊያን ለማድረግ ደፋ ቀና ስንል ያዬ በእውነት « እኔን ያዬ ይቀጣ» ያሰኛል ለአውሮፓዊያን።  አሁን  የአውሮፓ ማኅበረሰብ በተለይም  አብዛኛው የወጣቱ ክፍል የአባቶቹን ትቶ በተለየ አለም ላይ መኖር የጀመረ ይመስለኛል። ለዚህ ብዙ ምስክሮች አሉ። እነሱን መዘርዘ አስፈላጊም አይመስለኝም። ብቻ እኛ ኢትዮጵያዊያንስ ወደየት እያመራን ነው? ወደምዕራባዊያን  ወይም ወደቀደሙ አባቶቻችን .... ሁላችንም ራሳችንን ብንፈትሽ መልሱ ለሁላችንም ግልጽ ነው።

ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. 
ሃይደልበርግ፣ ጀርመን 

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Saturday, October 19, 2013

ጥበበኛዋ ነዳይ

(ዓለምነው ሽፈራው፣ ጥቅምንት 09፣ 2006 ዓ.ም.)፦
ዛሬ የጥቅምት ፀሐይ በጠዋቱ ብልጭ አለች እና ከወጣች የምትመለስ አትመስልም ነበር። እኔ  ከአንድ ባለእንጀራዬ ጋር ከቤት ወጣ ብለን ወደሱቅ ጉዞ ጀመርን። የምንፈልገውን ልንገዛ ከአንድ ሁለት ሦስት ሱቅ ተዘዋወርና ስንመለስ ጸሐያችንን እየሞቅን ምንም ተሽከርካሪ በማይኼድበት መንገድ ጉዞ ጀመርን። በዚያ ይጓዝ የነበረው ህዝብ መመልከት ልክ አመድ የተረጨ ጉንዳን ይመስላል። እኛም እየተጋፋን ጉዞአችንን ቀጠልን። ትንሽ እንደተጓዝንም አንዲት ጥበበኛ ነዳይ በጣም በጥበብ ትለምናለች።


ድምጽ አውጥታ ስለእግዚአብሔር እያለሽም አይደለም። ስለማርያም፣ ስለገብርኤል፣ ስለማንም እያለችም አልነበረም። እራሷን በአንዲት አፈር ሁሉ ተሸርሽሮ አልቆ ስሮቿ በሙሉ ፈጥጠው የሚታዪ እጽን መስላ እንጅ። ከሩቅ ሆነው ሲያዩት አንድ ቀለል ያለች ዛፍ ትመስላለች። ሲቀርቧት ደግሞ በበንድ ላላስተዋላት ለጌጥ የተሰራ ምስልን መስላም ታሳስታለች። እኔም ከባለእንጀራዬ ጋር እንዴ እንዚህ ነጮች ዛሬ ጀምረው የክሪስ ማስ ጌጣጌጥ መስራት መጀመራቸው ነው እያልኩኝ ወደ እሷ ቀረብን። ስንቀርብ ግን ብልጥ እና ብልህ የኔቢጤ ሆና አገኘኋት። በመንገዱ ከሚትመለመለው ሰው ግማሹ (በተለይ ወጣቱ ክፍል)   ቆሞ እሷን ይመለከታል። በሞባይሉም በካሜራውም ፎቶ ያነሳል፣ ይቀርጻል። እኔም እነሱን ልምሰል አልኩና ቆምኩኝ፤ ፎቶም ማሳንቴን ተያያዝኩት። 
እዚያ በቆምኩባቸው ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሰው እሷን በማየት  ፈታ ይልና ያለውን ጣል ያደርግላታል። እሷም እጆቿን በማንቀሳቀስ ትመርቃለች ወይም ታመሰግናለች።
እኔ ደግሞን ነዳያንን የማውቃቸው ስለእግዚአብሔር፣ ስለማርያም፣ ስለገብርኤል፣ ስለቅዱሳን ወ.ዘ.ተ. እያሉ በአንድ አካባቢ ብዙ ሆነው ሲለምኑ ነው። አንድም ቦታ ቢሆን እንዲህ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ሲለምኑ አላየሁም። በኋላም ከባለእንጀራዬ ጋር ለምን ተባባልን። ሁላችንም ከይመስለኛል ውጭ መልስ አልነበረንም። ለመሆኑ ለምን ይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ነዳዮ በአንድ አይነት ስታይል የሚለምኑት? ጥበብ ጠፍቶባቸው? ወይንስ ማኅበረሰቡ ጥበብን ስለማያደንቅ እና ሰሚ ተመልካች የለንም ብለው ስለሚያስቡ?  ወይንስ የሚለምኑት ስለቸገራቸው እና ሰዎች ሲለምኑ ስላዪ ብቻ?  እንደ እኔ ግን እንዲያው ጥበብን ቀልቀል እያደረጉ ቢለምኑ ሰውንም ፈታ ያደርጉታል፣ እነሱም የተሻለ ሊገኙ ይችላሉ ብየ አስባለሁ። ችግሩ እኛ ኢትዮጵያዊን አንዱ አዲስ ነገር ሲጀምር ሌላችን ተከትለን ያንኑ መድገም እንወዳለን። አንዱ ሱቅ ሲከፍት ሱቅ መክፈት። አንዱ መኪና ሲገዛ ሌላውም ያንኑ አይነት መኪና መግዛት። አንዱ ምግብ ቤት ሲከፍት ሌላውም ምግብ ቤት መክፈት። እናም ነዳያኖቻችንም እንደዚህ አይነት ጥበብን አንዱ ቢጀም ሁሉም ተነስተው ይህንን የሚጀምሩት ይመስለኛል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከነአሉን የከተማ መንገዶቻችን እንኳን ሙሉ በሙሉ በቆመ ምስል መሳይ ሰው ተሞልተው ማለፊ እንዳናጣም ስጋቴ ነው። ብቻ ጥበብ የተሞላበትን የልመና ዘዴ ብናስተምራቸው መልካም ይመስለኛል። 


ሃይደልበርግ፣ ብሔረ ጀርመን 

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Monday, October 14, 2013

ብቻ ልብ እንግዛ

Source: Facebook 
(ዓለምነው ሽፈራው - 04/02/2006 ዓ.ም. )፡
አላየሁም ብሎ ዳኛ ቢያጭበረብር፤
ግቡማ ግብ ነበር።
ያውም የለየለት አልፎ ከመስመሩ፤
ዳኛ ተወው እንጂ ቢያቅተው መቁጠሩ።
እግዜርም ይፈርዳል ኳሷም ገብታ አትቀር፤
ብቻ ልብ እንግዛ አሁን አንሸበር። 
ወገን አትረበሽ፤ ካለልክ አትዘን፤
ይችን ብናጣትም ፍትህ ተጓድሎብን፤
ብቻ ፍትሕ ተመኝ፣አሁን በወር እድሜ እናገኛታለን። 
ያች ግብ! ሁሉ የተመኛት፣
ሁሉ የሮጠላት፣ ሁሉም ያዘነባት፤
ፍርድ በመጓደል ብትቀር እንደዋዛ፤
እናገኛታለን ብቻ ልብ እንግዛ። 


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

አቶ› ተስፋዬ ገብረአብ እንደ ፓስተርነት እንደሚቃጣው አላወቅኩም ነበር?

(ዓለምነው ሽፈራው)፡ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባብም እንዲሉ፤ በመስከረም መገባደጃ ላይ ተስፍሽ ጉድ ይዞ ብቅ። ልክ መስከረም ሲጠባ «የስደተኛው ማስታዎሻ» ብዬ የከተብኩቱን ክታቤ አኮመኩማችኋለሁ ብሎ ብዙውን አማሎት እንደነበር ምስክር አይሻም። ተጠበቀ ወይ ፍንክች። በማተሚያ ቤት ተሳበበ። ብዙሃኑም (እኔንም ጨምሮ)  መስሎት ነበር።  
መስከረም ሲገባብደድ የተስፍሽ (መርዝ አዘል) ‹መጽሐፍ?› በየድረ ገጹ እና ማኅበራዊ ድረገጹ በነጻ መለቀቁን ሰማን። በነጻ በማግኜታችን ብዙዎቻችን ብንደሰትም፤ ሰው የደከመበትን እንዴት እንዲህ ያለ ምንም ዋጋ ይበተንበታል ብለንም ብዙዎች ተቆጭተዋል፣ ተቆጭተናል፤ ቁጭታቸውንም በድረገጽ እና በማኅበራዊ ድረገጾች የገለጽም ነበሩ። የሆነው ሆኖ መርዛማው መጽሀፍ መነበብ ጀመረ። ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ወደ አርባ የሚጠጉ እዕሰ ጉዳዮችን ይዟል። ታዲያ በሃያ ስምንተኛ ላይ የሰፈረው ርዕሰ ጉዳይ (ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት) ትንሽ ጆሮዬን ኮርኮር አደረገኝ እና አነበብኩት። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ተስፋዬ ወይ በደንብ እውነቱን በጻፈ፤ አለያ  ባያነሳው በተሻለው በነበረ። « እከሌ የሚባል እንዲህ ብሎ ጽፎ እንዲህ ሆኖ...ምንትሮስ  ቀባጥሮስ እያለ » ይልና የራሱን አመክንዮ በማከል እንደ ማጣቀሻ ሊያደርግ ይሞክራል። ወይ ካየ ማጣቀሻ፣ ማስረጃው ይኼው ባለን፤ ካላየ ደግሞ እንደ ጨዋነቱ (እዚህ ላይ ጨዋ ሲል የዋህ፣ ጥሩ መግባር ያለው ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል)  አርፎ በተቀመጠ። በዚያ ላይ እሱ የሚመስለውን ለራሱ ማመን ሲችል፣ ትውልዱን  የእንመን አይነት ጥያቄም ይቃጣዋል። በዚህም ሳይበቃው ቅዱሳኑ ትውልዳቸው ከዚህ ዘር ስለሆነ፤ ምንም ሳይሆኑ አልፈዋል፤ አሁን ግን ጥያቄ ልናሳባቸው ይገባል የሚል  ዘረኝነትንም ይሰብካል። ቅዱሳኑስ እንደእሱ እንደ እኔ ሰው በመሆናቸው (በግብር፣ በምግባር፣ በቅድስና ሳይሆን በተፈጥሮ) ከእከሌ ተወለዱ ይበለን። እውነት ነው የትውልድ ሃረጋቸው ይታውቃል። በቅድስናቸው፣ በአማላጅነታቸው የምናምነው ግን ኢትዮጵያዊ ስልሆኑም አይደለም። እሱ እንዳለው ከሸዋ፤ ከጎጃም፣ ከጎንደር ከትግራይ፤ ከወሎ፣ ከወላይታ፣ ከጉራጌ ወ.ዘ.ተ. ስለሆኑም አይደለም። ከግብጽ፣ ከሶሪያ፣ ከአርመን፣ ከሮም፣ ከእስራኤል ስለሆኑም አይደለም። ስለተሰጣቸው ቃልኪዳን እና ስለአማላጅነታቸው ነው። 
ለቅዱሳኑን ታምራት እንደማነጸጻሪያ የተጠቀመው ደግሞ ክብር ይግባውና የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ነው። አሁን ተስፋዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያ ውስጥ አለተውለደም እና  ኢየሰስ ክርስቶስ የኢትዮጵያ አምላክ መሆኑን እንጠይቅ ለማለት ትንሽ እንደቀረው እገምታለሁ። እምነት በዘር እና በትውልድ የሚሆን መስሎት። 
ይህም ብቻ አይደለም ተስፋዬ እስከአሁን  በቅዱሳኑ ላይ ጥያቄ ለማንሳት የጀመሩት (በህይዎት ያሉትን) ትውልድቸው ከዚህ ስለሆነ እና ትንሽ ቡጢን ስለቀመሱ አፋቸውን ዘግተው ቁጭ ብለዋል ይላል። እንደዚህ ሲል እሱ ከኢትዮጵያ ውጭ ስለሚኖር በቡጢ የሚለኝ የልም ብሎ አስቦ ይሆን አላውቅም። ለሱ እንደሚመስለው በዚች ምድር ቡጢ ባይቀምስም፤ እጥፍ ድርብ የሆነ ቅጣት እንደማይቀርለት ግን እርግጠኛ ነኝ። በማያውቀው ጉዳይ ገብቶ ለዘራው መርዝም በአጭር ጊዜ (ምናልባትም ከሳምንት ባነሰ ጊዜ) እራሱ በተናገረበት ብእር ትልቅ ቡጢ፣ ስጉማ እንደማይቀርለትም እርግጠኛ ነኝ።  ለሌሎች ርዕሱ ጉዳዮችም ቢጢዎች ብቅ ማለታቸው  የጀመረ ቢሆንም የበለጠ እንደሚነጉዱ ተስፋ አለኝ። 
አሁን ለእኔ አንድ ነገር ብልጭ ያለልኝ መሰለኝ። ተስፋዬ መጽሃፉን በማተሚያ ቤት ችግር ያሳበበው መጽሐፉ ቢታተም እና ወደ ገበያ ላይ ቢወጣ ብዙኃኑ ላያገኘው ይችላል፤ መርዜም በደንብ ሳይዘራ ይቀራል የሚል ስጋት አድሮበት ይመስለኛል። 
እኔ እኮ ‹አቶ› ተስፋዬ ገብረአብ እንደ ፓስተርነት እንደሚቃጣው አላወቅኩም ነበር? እኔ ለተስፋዬ የምመኝለት እንዲህ በማያውቀው እየገባ እውነትኛ ታሪክ ጻፍኩ ከሚለን፤ ነገሮችን በማጋነን የዘረኝነት ስብከት ከሚሰብክልን ይልቅ፤ እንደሚችለው ጥሩ ጥሩ ልብወለዶችን እንዲጽፍልን ነው። 

ቸር ያሰማን!


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)