(ዓለምነው ሽፈራው፡ ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ) ፡ መዛግብት የሚያስረዱን ቅኝ ግዛትን በ19ኛ እና በ20ኛ መቶ ክፍለ ዘመን እንደነበረ ነው። ብዙ የአፍሪካ ሃገራት በምዕራባዊያን በተለይም በአውፓዊያን ቅኝ ግዛት ውስጥ ወድቀውም ነበር። ምንም እንኳን ሀገራቱ ነጻነታችውን ያገኙ ቢሆንም ቅሉ በአስተሳሰብ ግን ዛሬውንም ከቅኝ ግዛት የወጡ አይደሉም። ይህን እጣ ፈንታ ሳይደርሳቸው ከቀሩት ሁለት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንደኛዋ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት መላለቀቅ አርእያ የሆነች አንዲት ሀገር ነበረች። የብዙ ሀገራት ጀግኞች እርሷን አይነተው ስለነጻነታቸው ታግለዋል። ታግለውም አልቀሩም ነጻነታቸውን መጎናጸፍንም ችለዋል። ይህችም ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ ቆራጥ የሆኑ ጀግና ሃይማኖተኛ ልጆች ስለነበሯት ቅኝ ገዥ ነን ብለው የዘመቱትን አውሮፓዊያንን አንበርክካ የመለሰች ነበረች። ልጆቿም ነጻነቷን ሲጠብቁ እንደቅኝ ገዢዎች በዘመናዊ መሳሪያ ሳይሆን፣ በሀገር በቀል መሳሪያዎች ግፋ ቢልም በቆመህ ጠብቀኝ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው። እነዚህ ጀግና ልጆቿም እናሰልጥናችሁ ሲላቸው እንደሚያሰየጥኗቸው አውቀው፤ አላፊ የሆነውን የነጭ ገንዘብ ሳያታልላቸው፣ ስለማንነታቸው ሲሉ ታግለዋል፣ ተፋልመዋል፣ አንበርክከውማል። የታሪክ ጸሐፊም አይደለሁም፣ የተነገረን ታሪክም ለመድገምም አይደለም። ነገር ግን ይህንን ላነሳ የወደድኩት ዛሬ ላይ የእኔ ዘመን ትውልድ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው በቅኝ ግዛት ሥር መሆኑን ሳስበው ስለሚቆጨኝ፣ ምናልባት ሰሚ ካለ ልብ ቢል ብየ ነው። ይህንንም የ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ቅኝ ግዛት ብየዋለሁ። ነገሩ እንዲህ ነው።
ያች ለአውሮፓዊያን ኃያላን ቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች ሀገር፣ ያ ለጣሊያን ያልተንበረከከ ጀግና ህዝብ ዛሬ እንኩላችሁ ብሎ እጁን እየሰጠ እንደሆነ ይሰማኛል። እንዴት የሚል አይጠፋም።
ነጪና ሃበሻ (ጥቁር ኢትዮጵያዊ ህዝብ) የተለያዩ ፍጥረታት ይመስል፤ ነጪ ማለት ከጥቁር በላይ ነው ብሎ የሚያስብ ብዙ ሰው እንዳለ ለማየት በሀገራችን ያሉ አንዳንድ ተቋማት ውስጥ ብቻ የሚሰራውን ማየት ከበቂ በላይ ነው። ለምሳሌ ያክል፡-
- አንድ ሃበሻ እና ነጪ በአንድ ላይ ወደ አንድ መስሪያ ቤት ቢሄዱ ቅድሚ ለማን እንደሚሰጥ ሁሉም ያውቀዋል። «ቅድሚ ለነጭ» የሚል ህግ ማን እንዳወጣ ባላውቅም፣ «ቅድሚያ ለሴቶች» እንደሚባለው ቅድሚያ ለነጮች ነው። ለምን ስትሉም «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጅ ነው» ነው መልሱ።
- ወደ አንድ ፍተሻ ወደ አለበት ቦታ አንድ ሃበሻና አንድ ጪ አብረው ቢገቡ፣ መከረኛው ሃበሻ የለበሰው እስኪቀደድ ድረስ ታሽቶ ይፈተሻል። ነጩ የሆነ እንደሆነ አይደለም ፍተሻ ቀና እንኳን ብሎ ማን ነህ የሚለው የለም። ለምን እኔ ብቻ እፈተሻለሁ ስትሉም «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጅ ነው» ነው መልሱ።
- ሃበሾች በሚዝናኑባቸው ሆቴሎች እና ፊልም ቤቶች በአጋጣሚ አንድ ነጭ ቢመጣና ወይ መቀመጫ ቦታ ቢጠፋ ወይም ያለው ለነጩ ባይጥመው የሆቴሉ ወይም የፊልም ቤቱ አስተናጋጆች በሙሉ በሃበሻው ላይ አሲረው እንደሚያስነሱትም በአይኑ ካየ ሰምቻለሁ። ለምን ብሎ ቢጠይቅም «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጅ ነው» ነው መልሱ።
- ጎበዝ እና ታታረ ሃበሻ የሚሰራው አጥቶ እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ፤ የእስያን ነጪ ማጋሰሥ ምን ይሉታል። ይህንን ለማየት በየዩኒቨርሲቲዎቻችን የተሰገሰጉ «መምህር» ነን ባይ ህንዳዊያንን (ጊዜ ቢፈቅድ ብዙ እንመለስበታለን)፤ በየታላላቅ የሃገር ሃብት የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እንደ ጉንዳን የሚትመለመሉ «መሃንዲስ» ነን ባይ ቻይናዊያንን ማየት ከበቂም በላይ አሰልች ነው። መከረኛው ሃበሻ ከአሥራ አምስት አመት በላይ ለፍቶ፣ ተንጠግሮ፣ የሀገር ሃብትን አባክኖ ተምሮ ቢያገኝ አንዲት ለእለት እንጀራ የማትበቃ ደምዎዝ የሚያስከፍልን ሥራ፤ ካልሆነ ደግሞ ኮብል ስቶን ጠራቢነት፣ ሲብስም ጎዳና ተዳዳሪነት የሚፈረድበት ለምን ይሆን? እውነት እውቀቱ ከህንዳዊያን እና ከቻይናዊያን የሃበሻው አንሶ ነውን? ህንዳዊያን እና ቻይናዊያንስ ልሂቃን ስለሆኑ ነው? እኔ ግን እላለሁ፤ መመካትም አይደለም ከ«ዶከተር» ነኝ ባይ ህንዳዊ ምንም ፊደል ያልቆጠሩት ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ሃበሾች ያስተምሩኝ። በ«ኢንጅነር» ነኝ ባዩ ቻይናዊ ከሚሰራ ይልቅ ሃበሻ የሰራው ይግደለኝ። ለምን እንዲህ ይሆናል ብሎ ለሚጠይቅም «እንዴ እነሱ እኮ ፈረንጅ ናቸው» ነው መልሱ።
- ነጪ ያደረገው ሁሉ ትክክል ነው ብሎ አሳቢ ሃበሻም አይጠፋም። ያንንም አደርጋለሁ በማለት ሌት ከቀን በማሰብ ብቻ ጊዜው የሚያጠፋ ብዙ አለ። ለምሳሌ በአነጋግገሩ፣ በአለባበሱ፣ በአካሄዱ ወ.ዘ.ተ. ነጪ መምሰል ብቻ ህልሙ የሆነ። ህልሙ ሁሉ የነጪን ሥራ። ነጪ ገደል ቢገባ እና ተከተለኝ ቢለው የሚከተለውም አይጠፋም ይመስለኛል። ለምን ቢሉ «እንዴ እሱ እኮ ፈረንጂ ነው » የሚል ይመስለኛል።
እንግዲህ ይህኔ ነው ነጪ በሃበሻ ላይ በሀገሬም አንደኛ ዜጋ፣ በሀገርህም አንደኛ ዜጋ፤ አንተ ግን በሀገርህም በሰውም ሀገር ሁለተኛ ዜጋ እያለ የሃበሻውን ሞራል የሚያንቋሽሽ። ታዲያ ይህ ቅኝ ግዛት መባል ይነሰው? ለዚህ ቅኝ ግዛትስ ማን ይሆን ተጠያቂው? ነጩ ወይስ ሃበሻው? እንደኔ ሃበሻ እራሱ ና ብሉ ጎትቶ ያመጣው ነው ባይ ነኝ።
ይህንን ትህትና ነው እንበለውን? እንግዳ አክባሪነት ነው እንበለውን? ምን እንበለው። ትህትና እማ ቢሆን አንተ ነጪ አንተ ጥቁር ነህ፤ አንተ ከአውሮፓ፣ ከአማሪካ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካ እንተ ደግሞ ከኢትዮጵያ ነህ ብሎ መከፋፈሉ ባልነበረ። አዛውንት ተቀምጦም ወጠምሻ ነጪ ቅድሚያ ባልተሰጠው ነበረ። እንግዳ አክባሪነት እንዳልለው እነዚህ ነጮች እስከ መቸ ነው እንግድነታቸው? እንግዳስ (ለጊዜውም ቢሆን ነጪን እንግዳ ብየዋለሁ) ታማኝ፣ ሃበሻ ደግሞ አጭበርባሪ የሆነው መቼ ነው? እንግዳ ሊያጭበረብር አይችልም ያለውስ ማን ነው? ... ብቻ አንዱም ምክንያት ሊሆንልኝ አልቻለም። ለእኔ ግን የዚህ ሁሉ በሃበሻ ላይ በደል ለትህትናም ለእንግዳ አካባሪነትም ሳይሆን «ያለጦርነት የመጣ ቅኝ ግዛት» ነው።
እኔ ሁለት የነጪ ሀገራትን እንዴት አንድን ሰው እንደሚያስተናግዱ «በመጠኑም» ቢሆን አይቻለሁ። አንዱም ሀገር ላይ አንተ የሀገሪቷ ዜጋ ሥለሆንክ ወደኋላ ቆይ፣ አንተ ደግሞ እንግዳ ስለሆንክ ቀድመህ ትስተናገዳለህ ሲል አላየሁም። ሁሉንም እኩል ለማድረግ ሲጥሩ አይቻለሁ። እውነት ነው የሃገራቸው ዜጋ ተቀምጦ ለሌላ ሀገር ዜጋ ሥራም ሲሰጡ አላየሁም። ከእነሱ የተረፈውን ለሌላው ግን ከመስጠትም ወደ ኋላ ሲሉም አላየሁም። እኔ ይህንን የሚያደርጉት የሌላውን ዜጋ ለማክበር ብለው ሳይሆን፤ ህጋቸው በራሱ ሁሉንም ሰው በእኩል እንዲያከብር ስለሚያዝዛቸው እና ህግጋቶቻቸውን ጠንቅቀው ስለሚያከብሩ ነው። እኛ የዛሬ ሃብሾች ግን «ወይ ራሳችንን አላስከበርን፤ ወይ እንደነጭች ህግጋቶቻችን አክብረን ሁሉንም ሰው በእኩልነት አላየን»። ዝም ብለን ሁል ጊዜ «እሱ እኮ ፈርንጅ ነው» እያልን በራሳችን ላይ ጉድጓድ ስንቆፍር እንውላለን።
ለዚህ መፍትሔውስ ምን ይሆን? (ለውይይት ክፍት ነው፤ ሐሳብ እንስጥበት።)
ሐይደልበርግ፣ ጀርመን
ለዚህ መፍትሔውስ ምን ይሆን? (ለውይይት ክፍት ነው፤ ሐሳብ እንስጥበት።)
ሐይደልበርግ፣ ጀርመን
(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)