Monday, December 24, 2012

ጨንጓራ ስምሽን ለውጠሽ መጣሽ?

       (አለምነው ሽፈራው)፦ አንድ የኔ ቢጤ ምስኪን የሀገሬ አርሦ አደር ወደ ከተማ ጎራ አለና  ምግብ ፍለጋ ወደ አንድ መጠነኛ ምግብ ቤት ገባ። እንደገባም የምግብ ቤቱ አስተናጋጅ ምን ልታዘዝ አለው። ያ ምስኪን አርሦ አደር ምን ምን አለ ሲለው፤ አስተናጋጁ በግርግዳው ላይ የተለጠፈውን የምግብ ዝርዝር አሳይቶ ምረጥ ብሎት ዞር አለ። በዝርዝሩ ውስጥም «ዱለት» የሚል አየና፣ ዱለት አዘዘ። ምግቡ ተሰርቶ ሲቀርብለት፣ ሲያይ  እርሡ የሚያውቀው ጨንጓራ ነው።  ከዚያም «አይ ጨንጓራ ስምሽን ለውጠሽ መጣሽ» አለ። ይህን ስል እንዲሁ ለቀልድ እና ለጨዋታ ብቻ አይደለም። ለቁም ነገር እንጅ። 
ዛሬ ዛሬ ተሐድሶዎችም ልክ እንደ ጨንጓራ ስም እየለወጡ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እስከ አሁን እነ አባሰላማ፣ አውደምረት፣ እና የመሳሰሉት የተሐድሶ መናፍቃን የጡመራ መድረኮች ክብር ይግባዉና መድኃኒታችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ፣ ልመናዋ አማልጅነቷ ይሰማል እንጂ እንዲሁ የማይቀርን እመብርሃን ድንግል ማሪያምን አታማልድም፣ ቅዱሳንን አያማልዱም፣ ገድላት ድርሳናት ልብ ወልድ ናቸው በማለት ሲዘባበቱ፣ ቅድስት አንዲት የሆነች በጌታችን ደም የተመሰረተች ኦርቶዶክሳዊት  ቤተክርስቲያናችንን ያረጅች ያፈጀች ናት በማለት ሲኮንኑ፣ እንዲሁም ብጹዓን ጳጳሳት አባቶቻችንን፣ በገዳም ያሉ አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን፣ ትጉህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን እና ማኅበራትን ያለ ስሙ ስም በመስጠት  ንጽህት ቅድስት የሆነች አንዲት ሃይማኖታችንን ለማፍረስ የምይፈነቅሉት ድንጋይ የማይምሱት ጉድጓድ የለም። አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ።  የቤተ ክርስቲያንን ልጆችም ለመንጠቅ ጥንብ እንዳየ አሞራ እያንጃበቡ ይገኛሉ። 

አሁን አሁን ምዕመናን፣ የቤተክርስቲያን ልጆች አላማቸውን አውቀውባቸው ራሳቸውን እና ሃይማኖታቸውን ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ፤ እንዲሁም  የነሱን የሐሰት በሬ ወለደ መረጃዎች የያዙትን የጡመራ መድረኮቻቸውን  ከማንበብ ሲቆጠቡ ስም እየለወጡ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።  ዛሬ ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ አጀንዳ የሆነውን የእርቀ ሰላም ጉዳይ እና የፓትርያሪክ ምርጫ በሆነበት ወቅት፣ ያልሆነው ሆነ፣ ያላዩትን አየን፣ ያለሰሙት ሰማን እያሉ፣ ጫፉን ይዘው ሲጎትቱ (ትክክለኛውን መረጃ ሳያገኘት ማለቴ ነው) ወሬ በማናፈስ ላይ ይገኛሉ።  አላማቸው አንድ እና አንድ ነው። በውሸት ተዋህዶን ለማጥፋት። መስሏቸው ነው እንጂ እርሷስ አትጠፋም፤ በአለት ላይ ተመስርታለች እና። 

ሲጅምሩ ቲፎዞ ለማፍራት፣ የአንባቢያንን ቁጥር ለመጨመር ኦሮቶድክሳዊ ይዘት ያላቸው ዜናዎችን፣ መረጃዎችን ማስነበብ ይጀመሩና ቀስ በቀስ ደግሞ ሸተት ሸተት ይላሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ «ተሐድሦ ሆይ ስምሽ ለውጠሽ መጣሽ?» ማለት ይገባል። 

መጽሐፍ ቅዱስ «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ። ፩. ተሰ. ፭፥፳»  ብሎ እንደሚነግረን  እኛም የምናነባቸው መረጃዎችን ምንጫቸውን ጠንቅቀን መመርመር ያስፈልጋል።  መልካሞችን መያዝ፣ ላልሰማም ማሰማት፣ ላልደረሰው ማዳረስ ( በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በፌስ ቡክ፣ በጐግል ፕላስ፣ በትዊተር..) ያስፈልጋል። አንዱ የሀገራችን አርቲስት (የሰው ለሰው- አስናቀ ማለቴ ነው)  «መረጃ አይናቅም አይደነቅም» አይደል ያለ። አዎ! እውነት ነው መረጃ አይናቅም አይደነቅም።  
«ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል» እንደሚባለው እነዚህ አቋማቸውን በውል ያለዩ የጡመራ መድረኮች ጥፋታቸው ከቀደምቶቹ የበለጠ ነው። የቀደምቶቹማ ታወቀባቸው፣ ተነቃባቸው። እነዚህ ግልግሎቹ ግን ወሬ ለማራገብ ማን ይሆናቸዋል?  
ሌላው የእነዚህን የተሐድሦ መናፍቃን የጡመራ መድረኮች  ሸር ማድረግ፣ ላይክ ማድረግ ለነሱ አንድ ጥቅም ያስገኛል። እርሡም በአብዛኛው ሁሉም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚጠቀሙት ስልት ለጓደኛ ጓደኛህ እንዲህ ሰራ፣ ይህንን ወደደ/ ላይክ አደረገ/  ወ.ዘ.ተ. በማለት ወሬውን በቶሎው ያደርሳሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ እነዚህን የሐሰት የመረጃ ቋቶች እና መድረኮች ላልሰማው፣ ላላየው እያሳወቅን በያዙት ሃሳብ እንዲጨነቅ፣ እንዲሁም ደግሞ እውነት ይሆንን እያለ እንዲጠራጠር (ብዙም እውቀት የሌለው ከሆነ ማለቴ ነው)  ያደገዋል።  እንዲሁም አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል አንድ እንደ አርአያ የሚቆጥረው ሰው አንድን ሥራ ሰርቶ ካየ ትክክል ነው ብሎ የመቀበል ዝንባሌው ያመዝናል። በዚህም እኛ ሸር፣ የምንወዳቸው  (በፌስ ቡክ ቋንቋ ላይክ) የምናደርጋቸው የጡመራ መድረኮችንም እንዲሁ እኛን የሚያዩ የዋሆች ይቀበላሉ። መጥፎ ሀሳብ ያላቸው ከሆነ ሳያውቁት ወደ ገደል እየመራናቸው ነው። መልካም ከሆነ ደግሞ በተቃራኒው። 
ታዲያ ይህ  መልካም ሥራ የምንሠራበትን ውድ ጊዜያችንን በመጨነቅ ማሳለፋችን፣ ብዙ እውቀት ለሌለው ደግሞ መጠራጠሩ ለተሐድሦአዊያን ትርፍ አይደለምን? ያውም ምንም ሳይሰሩ ያገኙት ትርፍ። ሥለዚህ የነሱን አንብቦ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማዳረሱ ጉዳቱ አደገኛ ነው እና እንወቅበት። 
ዲ.ን ኤፍሬም እሸቴ አደባባይ በተባለው የጡመራ መደርኩ «ከዜግነታዊ ጋዜጠኝነት አንዱ ጡመራ» ነው ብሎናል። እውነትን ይዞ መጦመር  ዜግነታዊ ጋዜጠኛ ያስብላል።  ቅሉ ግን በሀሰት ወሬ በማሳበቅ ሰውን ለማደናደናበር መሞከር ወንጀል ነው፣ ያስቀጣልም።  ጦማሪያንም አቋማችንን እንለይ።

«መጦመር እንጅ መቆመር ይቅር»

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

መልክአ ኢትዮጵያ

የድንግል ማሪያም የአሥራት ሀገር፤ የብዙ ቅዱሳኑ መጠጊያ፤ ሀገረ እግዚአብሔር ቅድስት ኢትዮጵያ። 
መልክአ ኢትዮጵያ

ሰላም ለዝክረ ስምኪ ኢትዮጵያ
ሀገሩ ለተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ፤ 
 ህዝብኪ ይዜምሩ እንዘ ይብሉ ሃሌ ሉያ።
 የሃይማኖት ድር የዉበት መለያ፤ 
ቀደምት ባለ ታሪክ የዓለም አርአያ።  

ሰላም ለአይንትኪ እለ ርእያ ፈጣሪ፤
ታምረ ኩሉ ገባሪ። 
ማዳን ፍቅሩን ላዩ፤
ከጸሎት ላልዘገዩ። 

ሰላም ለአእዛንኪ እለ ሰምዓ ፈጣሪ፤
በከመ ኮነ እግዚአብሔር መሐሪ፤
ቅዳሴው ሰዓታቱ፤
ላደመጡ ማኅሌቱ።
ሰላም ለአፉኪ ዘነበበ ወንጌሉ፤
እንዘ ይፌጽም ቃሉ፤
ሃሌሉያን ለለመደ፤
አኰቴትን ለወደደ፤
ቅኔ ዜማን ላወረደ። 

ሰላም ለገጽኪ ለለብሰ ልምላሜ፤
መልዓ ምሥጢር ወትርጓሜ፤
ለማይሽረው ዘመን እድሜ፤
የመልከኛ ሥያሜ፤
ለሆነው የውበት ፍጻሜ። 


ሰላም ለሀዳፍኪ እለ ሰፋ ሀበ እግዚአብሔር ህያው፤
ጸሎቱ እና ሙያው፤
ውዳሴ ነውና ግብሩ፤
ጌታሽ ነውና ክብሩ። 

ሰላም ለከርስኪ ዘአስረጸ ማዬ፤ 
ለጸሙ ሰብ ዘአስተዬ፤
ቅዱሱ ጸበል ለፈቀበት፤
የቅዱሳኑ አጽም ላረፈበት፤
ፈዋሹ እምነት ለተገኘበት።

ሰላም ለዘባንኪ እምዘባነ አለም ዘተሌለዬ፤
ጸዊረ ተሰዓቱ ቅዱሳን በሰቢከ ወንጌል ዘአብ፤
እንግዳን መቀበል ላልደከሙ፤
መካናትሽን ለተሸከሙ። 

ሰላም ለወልድኪ ያሬድ ማኅሌታይ፤
ወጣእመ ዜማ ቀዳማይ፤
 ግዕዝ እዝል ወአራራይ።
ምድርሽን በዝማሬ ላራሰ፤
የአፉን ቅኔ ላፈሰሰ። 

ሰላም ለወልድኪ አባ ተክለ ሃይማኖት
 ዘሖረ በሰናይ ፍኖት፤
እንደ መላእክቱ በክንፍ ለበረረ፤
ባከበረው ንጉስ ለከበረ፤
ጣዖታትን ለሰበረ።

ሰላም ለወልድኪ አባ ዜና ማርቆስ፤
ሐዋርያሁ ለክርስቶስ፤
እምዘመደ ተክለ ሃይማኖት ባህታዊ፤
ጥሪው ሰማያዊ፤
መንገዱ ሰላማዊ። 

ሰላም ለወለትኪ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ፤
እንበለ መጠን ዘበስዓ እበያ ወክብራ፤
ለተመሰገነች በጽድቅ ሥራ፤
እጅ ላልሰጠች ለዓለም ምርኮ፤
ለጸናች በአምልኮ። 

ሰላም ለመካንኪ ግሸን ደብረ ከርቤ፤
ለይዜምሩ ካህናት በፍሥሐ ወበይባቤ፤
ፍኖተ ብርሃን ይእቲ፤
 መንበረ መስቀሉ ዛቲ፤
መግቢያ በሯ አሐቲ። 

ሰላም ለመካንኪ መካነ ቅዱሳን ዝቋላ፤
እንተ ጸለዬ በአንቲ ገበረ መንፈስ ቅዱስ በማዕከላ፤
የቅዱሳኑ መፍለቂያ፤
የሰዓታቱ መድመቂያ።

ሰላም ለመካንኪ እንተ ተሰይመት ጻድቃኔ፤
በአት ይእቲ ለመናኔ፤
የድውያኑ መፈወሻ፤
የሀዘንተኞች ጭንቅ መርሻ፤
የዲያቢሎስ ድል መንሻ። 

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ላሊበላ፤
መካነ ትብስእት ወተድላ፤
የጸጋው ዘይት ሲፈላ፤
የተቀባው ልጅሽ፤
 ላነጸው መቅደስ በደጅሽ። 

ሰላም ለመካንኪ መርጦ ለማርያም፤
ደብረ ምሕረት ወሰላም፤
ለማይቋረጥባት እንጣኑ፤
ለሚጸልዩባት ቅዱሳኑ፤
ለፈለቁባት ምሁራኑ።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ዮሐንስ ሸንኮራ፤
እምነ ውስቴታ ደናግል ዘይዜምራ፤
ጸበሉ እውራንን የሚያበራ፤
የዮሐንስ ገዳም የመጥምቁ፤
የዘካርያስ ልጅ የጻድቁ።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ጽዮን አክሱም፤
እንተ ሀለወ ባቲ ታቦተ ጥንታዊት ወቅድም፤
ለጽዮን መኖሪያ ለከበረችው፤
ዳጎንን ለሰበረችው፤
ዳዊትን ካባ ላስጣለችው።

ሰላም ለመካንኪ ዋልድባ ሰላማዊት፤
አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፤
የአባ ሳሙኤል ገዳማቸው፤
ለሚተረክባት ገድላቸው፤
ላከበራት ጸሎታቸው።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ አሰቦት ቅድስት፤
መካነ ቡሩካን ውድስት፤ 
ጸሎት ላልራቃት ጠዋት ማታ፤
ለቀደሳት ጌታ።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ሊባኖስ ገዳሙ፤
እንተ አእረፈ ባቲ ለተክለ ሃይማኖት አጽሙ፤
ቅዱሱ ደብር መታሰቢያ፤
የመናንያን መሰብሰቢያ፤

የባለ ቅኔው ማሸብሸቢያ።

ሰላም ለመካንኪ መካነ ሰላም ደብረ ዳሞ፤

ይጸልዩ ባቲ አበው ቅዱሳን በአርምሞ፤
አረጋዊ በዘንዶ፤
በገደል ላይ ተረማምዶ፤
ለገደማት ጌታ ፈቅዶ።

ሰላም ለመካንኪ ምስራቀ ፀሐይ ዘደብረ ዘይት፤
መካነ ሕይዎት አማናዊት፤
ላሳደገችን በውብ ቋንቋ፤
ላስያዘችኝ የዜማ ቃል። 

ሰላም ለአቡኪ ወልደ ማርያም፤
ንጉሰ ነገስት ስቡህ በአርያም፤
ጠላትሽን ለተዋጋ፤
ለብርታሽ ክንዱን ለዘረጋ፤
ቅጥርሽን በእሳት ለዘጋ።

ሰላም ለእምኪ እመ ብዙኃን፤
ዛቲ ይእቲ ተድላ ብዙኃን፤
በአሥራት ለተሰጠሻት፤
በየዘመን ለጠራሻት፤
ስለ ፍቅሯ እናት ላልሻት። 
መልክአ ኢትዮጵያ። 






(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Wednesday, September 19, 2012

ዘመኑ ነው ጠማማ?

ትናንት ዛሬ ላይ ደርሶ፣
ተስተካክሎ ዉበት ይዞ፣
ስልጣኔው መጠቀና'ግድብ ጥሶ፣
ላይሆን ዛሬ ተመልሶ።
ዛሬም ትናንትን ሲኮንን፣
ትናንትም ጥንትን ሲባዝን።
እርስ በርሳቸው ሲናቆሩ፣
አንተ አንቲ ሲማረሩ።
አንዱ አንዱን ሲለው ክፉ፣
በቃላት ጥይት ሲናተፉ።
ሃጢአትም ዱሯን ስታደራ፣
የሞት ፍሬ ሲጎመራ።
እርካታ ሲጠፋ፣
የርኩሰት አድማት ሲንሰራፋ።
በሰው ልብ ውስጥ ምሬት ብቻ ሲንሰራራ፣
በንስሃ ራስን ማጠብ ቢያቅትማ፣
ሰዎች አሉ አላክሁ ዘመኑ ነው ጠማማ።
ግና ነገሩ ወዲህ ነው፦
ዛሬ እንደ ትናንቱ ከሰራን፣
ምግባር ከሃይማኖት ከያዝን፤
ዛሬም የትናንትን ላይመልሰው፣
ልጅ አባቱን ላይወክለው፣
ምንስ አዚሙ ሊያግደው።
የአባቱን ህግ አፍርሶ፣
የአምላኩን ትዕዛዝ ግድብ ጥሶ፤
የሃጢአት ሥራው የወዙ፣
ቢከፍለው ያ ደሞዙ፤
ቅርጥፎ ሰው ለሰው ካልተኛማ፣
እነውነት ዘመኑ ጠማማ?
ሰው ራሱን ካፈረሰ፣
መቅደስ ህይወቱን ካረከሰ፤
ፍቅር ከጠፋ ከሰው ጓዳ፣
ሌላው ለአንዱ ከሆነ የሃጢአት እዳ፤
የግብ ክምር ካሸከመው፣
የሞት ዝናር ካስታጠቀው፤
የወንድሙን ሰላም ከቀማማ፣
እነውነት ዘመኑ ጠማማ?
የሰው ልጅ በነበረው ቃኤል እንዲመስል፣
በቃላት ፈንታ ወንድሙን ቢያደማው።
በገበረው ሃጢአት በረከትን ቢያጣ፣
በችግር ቢገረፍ በእጦት ቢነጣ፤
በጽድቅ ፍኖት ፈንታ ሞትን ከሻተማ፣
እራሱ ነው ዘመኑ የትኛው ነው ጠማማ?
እኒያ ደግ አባቱን እየጠራ፣
የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ እያለ፣
በሃጢአት ጥቅም ተጠላልፎ እራሱን ካታለለ፤
ምርጫውን ካደረገ ከብርሃን ይልቅ ጨለማ፣
ኧረ ፍረዱኝ እናንተው ዘመኑ ነው ጠማማ?
ወዳጅነት ከቀረ፣
ጥላቻ ከከረረ፣
ፍቅር ከጠፋማ ፊትን ላያይ ከዞረ፣
ዘመኑ ምን ያርግ ሰው እንደ ትናንቱ ካልኖረ?
ኦ'ይ እ' እ'ም'...
ኩርችም ወይንን ወይንም በለስን ላያፈራ፣
ሰውነት ከሃጢአት ካላጠቡት ላይጠራ፣
ምንስ ፋይዳ ሊኖረው እናተው ዘመኑን ቢኮንኑ፤
የዚያ' የትናንቱ የፍቅር ሰውን ካልሆኑ።
እንደ ሐዋሪያት መኖር ካልቻልንማ፣
የበጎነት ውሉ ቁልፉ ከጠፋማ፣
በጥላቻ መንፈስ ሰው ወንድሙን ካማ፣
እስኪ ንገሩኝ' ዘመኑ ነው ጠማማ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ምንጭ፡ ድምጸ ተዋህዶ ሬዲዮ (http://dtradio.org/) መሰከረም 04 ቀን 2005 ዓ.ም. ፕሮግራም











(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Tuesday, September 11, 2012

እንቁጣጣሽ!!!

ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ
ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሲፈካ
ዝናም በሙቀት ሊተካ
ብርሃን ጨለማን ሲተካ
እንቁጣጣሽ!!!
የወራት ሁሉ መባቻ
የሁሉ ዓመታት መክፈቻ
ከቶ ለአንቺ የለሽ አቻ
እንቁጣጣሽ!!!
ርዶ የነበረው ምድሩ ረግቶ
ጠቁሮ የነበረው ሰማይ ፈክቶ
ሁሉ ሲታይ ተስፋ ሰጥቶ።
እንቁጣጣሽ!!!
ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ
ቤት ያፈራው ሁሉ ቀርቦ
ቤቱ ሁሉ አምሮ ተዉቦ
እንቁጣጣሽ!!!
...
አለምነው[መስከረም 1/2005]



(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Thursday, September 6, 2012

አንድ ህልም

ጥበብ የበዛባት ሀገር ተውልጄ አድጌ፤
እሻለሁኝ ለመማር መሰረቷንም ፈልጌ።
አንድ ህልም አለኝ ያለምኩት፤
እሮጣለሁ ያንንም ለማሳካት፤
እንደሚሰጥ አውቃልሁ ጥበብንም ለሚሻት፤
የእኔም ህልሜ ያችው ናት፤
ገጣሚ መሆን ጸሐፌ ተውኔት።

አለምነው [ነሐሴ 6/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Tuesday, August 28, 2012

እናቴ

ከቶ ምን ልክፈልሽ ውዲታ እናቴ
ውለታሽ በዘብኝ ለምስጋና የሚሆን ቃል አጣ አንደበቴ:: 
ከሰው በላይ እንድሆን ያየሽው መከራ
ቢነገር አያልቅም ለአለም ቢወራ፡፡
እራስሽን ጥለሽ እኔን ተንከባክበሽ
ከሰው በታች ሆነሽ እኔን አኮፍሰሽ
ቢያመኝ ተሰቃይተሽ ብሎም ተጎሳቁለሽ
እዚህ አደረሽኝ ከሰው በታች ሆነሽ
ውዲታ እናቴ እግዜር ጤና ይስጥሽ
እኔ በምን አቅሜ በምን ላመስግንሽ፡፡
ውስጤ ተቃጠለ እንባንም አነባሁ
በጣሙን ከበደኝ ውለታሽን ሳየው
እግዜር ዕድሜ  ይስጥሽ ከቶ ምን እላለሁ
ውዲቷ  እናቴ አመሰግናለሁ፡፡
                            ምንጭ:- የወል 

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, August 12, 2012

መሸነፍ ባይኖር ድል ማድረግ ባልነበረ!


ያኔ በባዶ እግር እንዳልተሰበረ፤
ምነው ዛሬ ወገን ሜዳው ባዶ ቀረ።
ያ ቀን እንዳለፈ ይችም ቀን ታልፋለች፤
ኦሎምፒክም ብትሆን ከርሞ ትመጣለች፤
ያ ድል ይደገማል በኢትዮጵያ ልጆች።
ስለዚህ አትሌቶች በተለይ ወንዶቹ፤
እናንት ናችሁና የሀገር ዋኖቹ፤
በርቱ ተበራቱ ሁሌ ሳትሰልቹ፤
ዛሬም ተስፋ አንቁረጥ የአበበ ዘሮቹ።
መሸነፍ ባይኖር ድል ማድረግ ባልነበረ!
አቤም በባዶ እግሩ ሮምን ባልዞረ፤
የአበበንስ ታሪክ ማን በመሰከረ፤
ስለ ኢትዮጵያ ማንስ በዘከረ፤
ግና በመሸነፍ ጅርባም ማሸፍ ስላለ፤
አቤ ታሪክ ሠራ በባዶ እግሩ እያለ፤
ዓለም እስከ ዛሬ ስለኢትዮጵያ ሲመሰክር ኖረ።
እስኪ እንጥይቃቸው ምን ነበር ታሪኩ፤
ምንስ ይዘው መጡ እን ኃይሌ ሲላኩ።
ይቻላል ይል ነበር ጅግናው አትሌት ኃይሌ፤
አሁንም ይቻላል አንሁን ባተሌ፤
እንደ አባት ይምከረን ኃይሌም ቢሆን ሁሌ።
እናም አትሌቶቹ የሀገር ዋኖቹ፤
የኢትዮጵያ ልጆች የአበበ ዘሮቹ፤
ያ ቀን ይመለሳል አሁንም አትሰልቹ፤
ታሪክ ይደገማል አሁንም አትሰልቹ።

ማስታወሻነቱ፦ በነሐሴ 6/2004 ዓ.ም. ለታጣው የማራቶን የኦሎምቲክ ድል፣ በውድድሩ ለተሰለፉት አትሌቶች እና ለመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን አበበ ቢቄላ ይህንልኝ። 
አለምነው [ነሐሴ 6/2004 ዓ.ም.]


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Saturday, August 11, 2012

ታዘብኳችሁ!



ወገኔ ምን ነካችሁ?
እንዲያው በብዙ ታዘብኳችሁ።
ፌስቡክን መሉ እንዳልነበር ጩኸታችሁ፤
ኢሜል ሙሉ እንዳለነበር ድጋፋችሁ፤
ብሉግ ሙሉ እንዳልነበር እልልታችሁ፤
ታዲያ ትናንት ምን ነካችሁ?
እንዲያው በብዙ ታዘብኳችሁ።
ሥዕል አድህኖ ስላያችሁ?
ደግሞም ምትሃት ነው ትላላችሁ፤
ለማን ነው ይሆን ድጋፋችሁ?
ለአትሌቶቹ ወይስ ለኢትዮጵያ ለሀገራችሁ ።
ለማን ይሆን ወርቁ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለመሰረት?
ለማን ይሆን ስሙ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለመሰረት?
አቋማችን አንድ ይሁን ለዓላማ ለአንድነት፤
ጹኑ አቋምም ይኑረን አንድ ኢትዮጵያዊነት።
ወርቁም ቢመጣ ለኢትዮጵያ ነው፤
ሥሟም ቢጠራ ኢትዮጵያ ነው፤
ታዲያ ወገኔ ሽሙጡ ምንድን ነው?
አዎ! መሰረትም ላቧ ጠብ ያለበት ደምወዟ ነው፤
ያም ሆነ ይህ ክብሩ ግን ለኢትዮጵያ ነው።
እናም ወገኔ አትሸወድ፤
አንዱም በአንዱ ላይ አይፍረድ፤
ድጋፋችን ከሰው ብቻ ወደ ኢትዮጵያም ይውረድ።
አዎ! ታምናለች፣ ያመነችበትንም ሰርታለች፤
ታዲያ መሰረት ምን አጠፋች?
ሥዕል አድህኖ ስላሳየች፤
ጣኦት አምላኪ ተባለች።
ግን ይህ አይደለም አምልኮ ጣኦት፤
ለቆሙበት አላማ ያመኑበትን መስራት፤
ደግሞም ከሁሉ በአምላክ እናት።
ታዲያ ለምን ነው ይህን ያክል ሽሙጡ፣
በውስጠ ወይራ ቃላትን ልውውጡ።
አዎ! አትሌቶቻችን ናቸው የእኛ ሞገስ የኛ አርዕያ፤
አዎ! አትሌቶቻችን ይገባቸዋል ክብር፣ ስለሆኑ ለኢትዮጵያ ማስጠሪያ፤
ድጋፋችን ግን ለሰው ሳይሆን ይሁን ለኢትዮጵያ።
ለአትሌቶቻችን እስኪ እንስጣቸው ሞራል፤
ክብር ለሚገባው ክብርም ቢሆን ይገባል።
ታዲያ ወገኔ ለምን አላደረግንም ይህን?
ፍቅራችንስ፣ ከአንገት በላይ ለምን ይሆን?
ፉጨታችን ለሰው ብቻ ለምን ይሆን?
ምን አመጣው  ሃሜትን?
ያየነው ባህሪ ከዘወትር ስለተለየብን፤
ወገኔ አትሳሳት ድጋፍክም ቢሆን፤
ለሀገር እንጂ ለሰው ብቻ አይሁን።
ታዲያ ወገኔ ምን ነካችሁ?
ፍቅራችሁንም ቀነሳችሁ?
እኔስ በብዙ ታዘብኳችሁ።
እንዲህ ነበር ወይ ወጉ፤
ላሸነፈ ሽልማቱ፣ ወርቅ ላመጣ ማዕረጉ፤
አቤት ባየን መለስ ብለን ከአባቶቻችን፤
ብናነብስ ብንጠይቅስ ምን እንደነበር ታሪካችን፤
ፍቅር እንጂ ማማት አልነበረም ባህላችን።
ተው ወገኔ ቆም ብለህ አስብ፤
ታሪክህንም ጠይቅ አንብብ፤
ከደመቀው አትዝፈን፤
እርስ በርስህ አትጨክን፤
ለኃጥአን የመጣው ለጻድቃን እንዳይሆን፤
ፍቅራችንም ከአንጀት እንጂ ከአንገት አይሁን።
እናም ወገኔ! እናስተውል፤
ዛሬ ብንተዛዘብ ቀንም ያልፋል፤
የጭንቅ ቀንም ይመጣል፤
ታዲያ ያኔ ምን ሊባል?
ጥሩነሽ ብቻ ትሩጥ አይባል፤
አይቀርም እኮ በመሰረት አደራ መጣል።
ስለዚህ ወገኔ ተጠንቀቅ፤
የምትናገረውን የምትጽፈውንም እወቅ፤
ከዚያም ይሆናል የተባረከ ወርቅ።
አለዚያ ግን ወገኔ፤
እንደታዘብኩህ እኔ፤
ጩኸት እንጂ የለምህም ወኔ።

ማስታወሻነቱ፦ ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል በቅ.ድንግል ማሪያምን ስዕለ አድህኖ ላይ እምነቷን በመግለጿ ሳያውቁ ሽሙጥን ላበዙባት ድል አድራጊዋ መሰረት ደፋር
አለምነው [ነሐሴ 5/2004 ዓ.ም.]









(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Friday, August 10, 2012

ማለዳ ሲቀና እስከ ማታ ጤና!



ማለዳ ሲቀና እስከ ማታ ጤና!
 ዛሬም ተደገመ! በራስ መተማመን መሰረት ነውና።
 እምዬ ኢትዮጵያ ስንት ልጆች አሉሽ?
 እንደ ንብ ተናድፈው በዓለም ያስጠሩሽ፤
እንደ አንበሳ ታግለው ወርቅም ያመጡልሽ፤
ቁጥራቸው ብዙ ነው ፍቅርን ያድልልሽ።
በባዶ እግር ተሩጦ ተጥሎ መሰረት፤
ዛሬም ወርቅ አገኘን በአምላክ ቸርነት።
ባንዲራውም ከፍ አለ፣
መዝሙርሽም ተዘመረ፤
እንደ ሁሌው ተጨፈረ።
አንቺ ሀገሬ፣ ልጆችሽ ናቸው መንፈሰ ብርቱ፤
አንዲቱ ብትቀር ሌላይቱ፣
አልበገርም ባይነቱ፣
ወርቅን አስገኘሽ ዛሬም እንደ ጥንቱ፤
ሁሌም አይቀር ስምሽም መጠራቱ። /2/
 የታደልሽ ሀገር ሥመ ጥሩ፤
ልጆችሽ ደፋር ሞት አይፈሩ፤
ይኖራሉ ዘላለም ስምሽን ሲያስጠሩ።
ይህ አይደለም እንዴ የአባቶሽ ብሒል፤
ከቤት ዶሮ ሲታረድ ከሜዳ ቆቅ ይገባል፤
ገና ይደገማል! ስምሽም ለዘላለም ይጠራል።
ሲታገሉ ውሎ ሲስቅ አዳሪ፤
የእናት ሀገሩን ስም በዓለም አስጠሪ፤
አምላኩን የፈራ ሰውንም አክባሪ፤
 ብቃቱን በሥራ በሰው አስመስካሪ፤
 መሰረት ጥሩነሽ ቀጥይበት ሥሪ። /2/ 

ማስታውሻነቱ፡- ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል እና ድል አድራጊዋ መሰረት ደፋር
አለምነው [ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, August 5, 2012

አዎ ይደገማል!

አዎ ይደገማል!

አዎ ይደገማል!
እማማ ኢትዮጵያ ኩሪ ይገባሻል፣
እንደ ቲቂ ያሉ ልጆችን ወልደሻል። 
ወርቅማ ወርቅ ነው፣ በብርም ይገዛል፤
ይህን ክቡር ስምሽ ከቶ ማን ያስጥራል፤ 
ልጆችሽ እያሉ ዘላለም ይጠራል፣ አዎ! ይደገማል። 
ገና መች ተነካ አዎ ይደገማል! 
እማማ ኢትዮጵያ ክብር ለባንዲራሽ፤
ሰላም ለልጆችሽ፣ አምላክ ያድልልሽ፤ 
ስምሽን አስጠሩት ወርቃማ ልጆችሽ። 
ሁሉም በአንደበቱ ቲቂ ቲቂ እያለ፤
በልቡም አምላኩን እርዳቸው እያለ፤
ሰዓቱም ተገፋ፣ ርቀቱም አጠረ፣ 
ኮመንታተሩ ሳይቀር ገላና ገላና ከኢትዮጵያ እያለ፤
ቲቂ ብቅ ስትል፣ እልልታው አየለ። 
አዎ ይደገማል! 
ስምሽም ዘላለም በአለም ይጠራል። 


ማስታውሻነቱ፡ ሐምሌ 29/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የማራቶን ድልና ድል አድራጊዋ ቲቂ ገላና።

አለምነው [ሐምሌ 29/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

እውነትም ጥሩነሽ

እውነትም ጥሩነሽ

ጠላትሽ በሙሉ ውድቀት ቢመኝልሽ፤
አንቺ ግን አንቺው ነሽ፣ ሁልጊዜም ጥሩነሽ፤
ቤቢይ ፌስ ኪለሯ፣ እወነትም ጥሩ ነሽ።
ትንሹም ትልቁም ህጻን ልጅ አዋቂው፤
በውስጥም በውጭም ባህር ማዶም ያለው፤ 
ጥሩነሽ እያለ ልቡንም በተስፋ ቢሞላው፤
ወርቁም አልቀረበት ኩራትም ተምሰማው፣ ባንዲራውን ሲያየው፤
ያ! ሰው ወዳድ ወገንሽ፣ መክሮ ያሳደገሽ፤ 
ሁሉም ደስብሎታል፣ አንቺም ደስ ይበልሽ። 
እማማ ኢትዮጵያ፣ ልጆሽ የት አሉ? 
እንደነ ጥሩነሽ፣ እንደ ቀነኒሳ፣ እንደ ኃይሌ ያሉ፤
ወርቁማ ወርቅ ነው ስምሽን ያስጠሩ። 


ማስታወሻነቱ፡ በሐምሌ 27፣ 2004 ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል እና ድል አድራጊዋ ጥርነሽ
አለምነው  [ሐምሌ 27/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Saturday, April 7, 2012

ታሪክ ወመዝሙር ዘሆሳዕና

የሆሳዕና በዓልን አስመልክቶ የተለያዩ የ ቤተክርስቲያን መምሀራን እንዲህ ያስተምራሉ። ከጎኑ ያለውን ማያያዣ /ሊንክ/ በመከተል ዝርዝር ትምህርቱን እና መዝሙሩን ማግኘት ይችላሉ።

  1.  "አንች የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉሥሽ በእህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ ዮሐ.12፥15፡፡"   «ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡» ዮሐ.12፥13     ዝርዝሩን ከማኅበረ ቅዱሳን (በዲ/ን በረከት አዝመራው)
  2.  ”አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺይመጣል” ዘካ 9፥9  ስለ ሆሳዕና በዓል ሰፊ ታሪክና ስርዓት... ዝርዝሩን ከማኅበረ ቅዱሳን የአውሮጳ ማዕከል (በኤርምያስ ልዑለቃል)
  3. ህጻናትና የሚጠቡ ልጆች እንዲሁም የቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥተው "ሆሳዕና በአርዕያም፤ ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት" ብለው አመሰገኑት።  የሆሳዕና ታሪክና ምሳሌ በድምጽ ... ዝርዝሩን  ከተዋህዶ ሚዲያ (በመላክ ሰላም ቀሲስ ድጄኔ ሺፈራው) --> ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው -->ሆሳዕና ታሪክ እና ምሳሌ  ላይይጫኑ
በበዓሉ ዕለትም በቤተክርስቲያናችን እነዚህ ይዘመራሉ
ከበዓሉ ረዲኤትና በረከት ያካፍለን።  አሜን!!!

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Wednesday, February 8, 2012

"እናትዬ"

ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀንሽ ይዘሽ፣
በዚህም ሳይበቃ በምጥ ተሰቃይተሽ፣
ሦስት ዓመት አጥብተሽ፣ ከጡትሽ መግብሽ፣
ደከመኝ ሳትይ በአንቀልባም አዝለሽ ፣
በፍቅር ያሳደግሽኝ ፍቅርሽን ለግሰሽ፣
እናትዬ  ከቶ ምን ልክፈልሽ?

       አንቺን እየራበሽ እኔን ያበላሽኝ፣
       አንቺን እየጠማሽ እኔን ያረካሽኝ፣
       አንቺ እየበረድሽ እኔን ያለበስሽኝ፣
       አንቺን እያመመሽ እኔን ያፅናናሽኝ፣
       ውዲቷ እናቴ  አብዝተሽ ናፈቅሽኝ።

አንቺ ሳትማሪ እኔን ያስተማርሽኝ፣
ከተፈጥሮሽ ጥበብ እውቀት ያካፈልሽኝ፣
መክርሽ ገስጸሽ ለዚህ ያደረስሽኝ፣
ለወግ ለማዕረግ ለክብር ያብቃሽኝ፣
ወላጂቷ እናቴ ዘላለም ኑሪልኝ።



(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, January 29, 2012

«ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማሪያም የዐጽብ ለከሉ፤ ሞት ለሟች ይገባል፣ የማሪያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል»


«ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማሪያም የዐጽብ ለከሉ፤ ሞት ለሟች ይገባል፣ የማሪያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» ቅ. ያሬድ 
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በዓል ዕረፍት በሠላም አደረሰን!!!

በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

/ነግሥ ዚቅ፤ የጥር 21 አርኬ/

እመቤታችን በዚህ ምድር ላይ ሦስት ዓመት ከእናት አባቷ ቤት አስራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን ፀንሳ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦሥት ወር ከጌታችን መድኃኒታችን ጋር አስራ አምስት ዓመት ከዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በስድሳ አራት ዓመቷ ጥር 21 ቀን በ 49 ዓ.ም ገደማ አረፈች፡፡ 

እመቤታችን በዐረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሥጋዋን ሊቀብሩ ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘው ሲሄዱ ለተንኮል የማያርፉት አይሁድ እንዲህ አሉ «ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ ተነሣ እያሉ ሕዝቡን አስኮበለሉ አሁን ደግሞ እናቱን ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያውኩ ሥጋዋን እናቃጥል» ተባብለው ከመሀከላቸውም እንደ ጎልያድ በጉልበቱ የሚመካ ታውፋንያ በሚሉት የጎበዝ አለቃ እየተመሩ ወደ ሐዋርያት መጡ፡፡ ታውፋንያ የተባለው ትዕቢተኛ የእመቤታችን ሥጋ ያረፈበትን አጎበር /አልጋ/ ከሁሉ አስቀድሞ ያዘ፡፡ ወዲያው ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ሁለት እጆቹን በሰይፍ ቀጣው፤ እጆቹም አጎበሩ ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ «እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንም …´ 1ሳሙ. 26-9 ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመናት «የእውነተኛ አምላክ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ ይቅርታ ታደርጊልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ» አላት፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት እንደቀድሞው ደኅነኛ እጅ ሆነለት፡፡

ከዚህ በኋላ መልአክ ዮሐንስን ጨምሮ የእመቤታችንን ሥጋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሩት፡፡ ሐዋርያት «የእመቤታችንን ሥጋ አግኝተን በክብር የምንቀብረው መቼ ይሆን» እያሉ ይናፍቁ ጀመር፡፡ 

ዮሐንስም ከተመለሰ በኋላ እንደምን አለች? አሉት፡፡ ዮሐንስም «እመቤታችንማ ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ከዚያም ሱባኤው እሑድ ያልቃል እሑድ አምጥቶ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ ማከሰኞ ተነሥታለች «ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ» ያሰኘው ይህ ነው፡፡

ስለ እመቤታችን ትንሣኤ አባቷ ዳዊት በመዝ.131-8 «አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት» በማለት ለአምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ የሆነችው አማናዊት ታቦት ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ልጇ ሁሉ እርሷም ከሙታን ተለይታ እንደምትነሣ ተናግሯል፡፡ 

ስሎሞንም እንዲህ ብሏታል፡፡ «ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ንይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ÷ ዝናቡም አልፎ ሄደ ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ ÷ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ መዐዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ» /መኃ.2-10-14/፡፡ ይህን ኃይለ ቃል ሲተረጎም በውስጡ ብዙ ምስጢራዊ ነገሮችን ያቀፈ ነው፡-

«በክረምትና በዝናብ» የተመሰሉ የእመቤታችን መከራዋ ናቸው፡፡ ካህኑ ስምዖን «በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል»/ሉቃ.2-35/ እንዳላት፡፡ አሁን ግን ያ የመከራ ክረምትና ዝናብ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ማለፉን ፤

«አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ» ሲል የሐዋርያት ድምፅ ወይም ስብከት በምድር ላይ ሁሉ መሰማቱን ነው፡፡ ዳዊት በትንቢቱ /መዝ.18-4/ «ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ» እንዲሁም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ወደ ዓለም ሁሉ ሒዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ»/ማር.16-15/ ያለው ቃል ተፈፀመ፤ 

«የዜማ ጊዜ ደረሰ» ዜማ ያለው መከሩን ነው፡፡ መከር የፍሬ ጊዜ ነው ፡፡ ስለሆነም የሐዋርያት ስብከት ፍሬ አፈራ፤ 

«በለሱ ጎመራ» በጎ ምግባር የሌላቸው ሰዎች ምግባር መሥራት ጀመሩ፤

«ወይኖች አብበዋል መዐዛቸውንም ሰጥተዋል»፡- በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ፣ መዐዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ጀመሩ፣ ወደጄ ሆይ ተነሽ እያለ ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን እንደጠራት በሚያስደንቅ ሁኔታ ሰሎሞን ተናገረው ፤ እመቤታችን በሦስተኛው ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳንጠብቅ በአምላክ ፈቃድ ተነሣች ፡፡ 

ቶማስ አልነበረም ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት «ወፈቀደ ይደቅ እም ደመናሁ»፡፡ ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ / «ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም»/ዮሐ.20-25-25/ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ ብሎ፡፡ እመቤታችንም «ዐይዞህ አትዘን ወንድሞችህ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም አንተ ዐይተሃል ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው» ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ እርሱ ሔዶ ለሐዋርያት የእመቤታችንን ዕርገት አበሰራቸው፣ ለምልክትም የያዘውን ሰበን /መቀነት/ ሰጣቸው እነርሱም ለበረከት ተካፍለው ወደየ ሀገረ ስብከታቸው ሔደው በዓመቱ ቶማስ ትንሣኤሽን ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው ሱባኤ በነሐሴ መባቻ ገቡ በ16ኛው ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ አቁርቦአቸዋል፡፡

ሞት ለሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ ፈንታ ቢሆንም ከሞተ ሥጋ እናቱን ማስቀረት ሲችል፣ አለማስቀረቱ የፈጣሪ ፈታሒነቱን ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ቅዱስ ያሬድ እመቤታችን የአምላክ እናት ስትሆን ዕረፍቷ የሚያስደንቅ መሆኑን «ሞት ለሟች ይገባል፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት የዘመረው፡፡
የድንግል ማሪያም አማላጅነት አይለየን። 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Thursday, January 19, 2012

ትዝታ

ዕለቱ ሐሙስ ወርሁ የአስተርዕዮ ዘመን ነው።  የፈስቡክ ግውደኞቼ "አትሄድም እንዴ"፣ እያሉ ከዚያም ከዚያም ጥሪያቸውን ቀጠሉበት። እኔ ያሉበት ደግሞ እንሂድ ቀርቶ ሲበሉ ብደረሱ እንኳን  እንብላ የማይባልበት ነው። ይህን የእንዉጣ ድምጽ ስሰማ ምን አለ  ስል  ከልቤ አንድ ነገር  ከተፍ አለ። "ከተራ እና ጥምቀት "።

ሁሉም አንደየ አቅሙ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እያለ  አለኝ የሚለውን ለብሶ፣ ከየ ቀየው ብቅ ብቅ ሲል ያለዉ ድባብ አጀብ  ያስብላል። ግሩም የኢትዮጵያዊነት ባህል።  ከዚያም ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ፣ የማትለየዋ ቅድስት ወደሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ከርስቲያን ጉዞው  ይጀመራል።  ጳጳሳቱ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ ታቦቱን ይዘው ከቤተ መቅደሱ ብቅ ሲሉ፣ ይህ ህዝብም ከመዘምራኑ ጋር በመሆን "ታቦት በዉሥቴታ" እያለ ታቦቱን በማጀብ ጉዞዉን  ወደ  ባህረ  ጥምቀቱ ይገሰግሳል። አቤት ይህን ጊዜ ያየው። ዓለም ቅልጥ ትል ይሆናል። በዓሉ መንፈሳዊ መሆኑ ተረስቶ እንድያው ጭፈራዉንም ያስነኩታል። አዛዉንቱ፣ ወጣቱ፣ ህጻናቱም ሳይቀር ታቦቱ የሚሄድበትን ቦታ ምንጣፍ በማንጠፍ፣ ቀጤማ በመጎዝጎዝ፣ ሽቶ በመረብረብ ሽር ርጉድ ሲሉ አለማየት ነው። ሊቃዉንቱ፣ የሰንበት ተማሪዎች የሚዘምሩት መዝሙርማ ነፍስን ዉስድ አድርጎ፣ በምድር ቀርቶ ከሰማይ መላእክት ጋር ያለ ነው የሚያስመስለው። እንዲህ እየተሆነ የየአድባራቱ እና ገዳማቱ ታቦታት በአንድነት ከባህረ  ጥምቀቱ ይደረሳል። ታዲያ ይህ በዓል፣ ባህል እንኳን በህይዎት ላለ በመቃብርም እንኳን ትዝ ይላል።  
በዚህ ጊዜ ወጣቶቹ ሌላም ነገር አላቸው። ሎሚ ዉርወራ። አንድ ጎረምሳ የምዎዳት ካለች ሎሚ፣ እንቦአይ ይወረውራል። ኮረዳዋም ብትሆን ይምትዎደው ካለ ከመወርወር አትቆጠብም። ብዙ ሰዎችም በንደዚህ አይነት ሁናቴ ተገናኝተው ኑሮአቸውን የሚገፉ አሉ።
ከዚህ በሁአላማ ሁሉ በዚያም በዚያም ወከባ ይሆናል። ሌሊቱን በሙሉ ካህናት ሊቃዉንቱ ስብሐቱን እንደ ዝናብ ስያፈሱት ያድሩና ወደ ቅዳሴ ይገባሉ። ሕዝቡም የቻለ ከታቦቱ አብሮ ሌሊቱን ያልጋዋል። ያልቻለ ደግሞ ከቤቱ አረፍ ብሎ ያድርና የአህያ ሆድ ሲመስል ጎዞዉን ወደ ታቦቱ ያደርጋል።  ቅዳሰዉም ሲነጋ ያልቅና ወደ ጥምቀት ይሄዳል። ከዚህ በሁአል ያለዉን ትርምስ አታንሱት። ያም ያም ከበረከቱ ለማግኘት ግፊዉ በስመ አብ። ለነገሩ  ግፊዉ የሚጀምረው ገና በጠዋቱ ቅዳሴው ሳይጠናቀቅ ነው። ቢሆንም ግን በረከቱ  ብዙ ዉሃ በማግኘት ይመስል፣ ጥምቀቱ ሲጀመር ያለዉን  ግፊ ተዉት። 
በዓሉ የሚከበረው ለእኛ ሲል ወደዚህ ዓለም መጥቶ በባህረ ዮርዳኖስ የዕዳ ደብዳበያችንን የቀደደበት የጌታችን የዚየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው። በዚህ በዓል ምስጢረ ስላሴ የተገለተበትም ነው። ዝርዝሩን በዚህ እለት ሊቃዉንቱ ሲያስተምሩት ምን ያክል አስድናቂ     ነው። ዮሐንስ በባህረ ዮርዳኖስ ክርስቶስን ሲያጠምቅ፣ ከሰማይ በደመና አብ "የምዎደው ልጄ ይህ ነው" አለ። መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል መጥቶ በላዩ ላይ አረፈበት። በዚህ መልክ ነው አንድነት ሶስትነት የተገለጠው። ትልቅ የሆነዉን ትምህርት ከሊቃዉንቱ ቃል እንስማ።
እንዲህ እንዲህ እያለ ወደ በዓሉ እለት ከረፋዱ አምስት ስድስት ሰዓት  ይደረሳል። ከዚያም ያ አምሮበት የወጣ ሕዝብ እንዲያ እንዳለ፣ ታቦቱን እንዳመጣ ዝማሬው፣ ምንጣፍ ማንጠፉ፣ ቀጤማ መጎዝጎዙ፣ ሽቶ መረብረቡ ሳይጎአደል ከቤተ መቅደሱ ያደርሰዋል። ከዚህ በሁአላ ነው ወደቤት መመለስ ያለው። 
እኔም በአቅሜ ከዚህ ሁሉ እካፈል ነበር። ነገር ግን  በዚህ ዓመት ለአይን እንኳን ማየት አልቻልኩም። ምን ይደረግ እንጀራ ሆነና። እንዲህ እያልኩኝ ከርሞ ሁለት ዓመት አድርሰኝ ብዬ በመሳል፣ ትዝታዬን ልቆአጭ። 

ከበዓሉ በረከትም ይድረሰን!!! አሜን!!!

በዕለቱ ከሚዘመሩ መዝሙራትና ትምህርቶች በከፊል: 




(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, January 15, 2012

Positive Inspiration Quotes

"Yes, I have made lots of mistakes; because Life didn't come with instruction."

" To your mind be gentle,
  To your life be honest,
  To your heart be true,
  To your soul be kind! "



The Ten Rules For Being Human.
  1. You will receive a body. You may like it or hate it, but it’s yours to keep for the entire period.
  2. You will learn lessons. You are enrolled in a full-time informal school called, ‘life’.
  3. There are no mistakes, only lessons. Growth is a process of trial, error, and experimentation. The ‘failed’ experiments are as much a part of the process as the experiments that ultimately ‘work’.
  4. Lessons are repeated until they are learned. A lesson will be presented to you in various forms until you have learned it. When you have learned it, you can go on to the next lesson.
  5. Learning lessons does not end. There’s no part of life that doesn’t contain its lessons. If you’re alive, that means there are still lessons to be learned.
  6. ‘There’ is no better a place than ‘here’. When your ‘there’ has become a ‘here’, you will simply obtain another ‘there’ that will again look better than ‘here’.
  7. Other people are merely mirrors of you. You cannot love or hate something about another person unless it reflects to you something you love or hate about yourself.
  8. What you make of your life is up to you. You have all the tools and resources you need. What you do with them is up to you. The choice is yours.
  9. Your answers lie within you. The answers to life’s questions lie within you. All you need to do is look, listen, and trust.
  10. You will forget all this.
-Dr. Cherie Carter-Scott, If Life is A Game, These Are The Rules

Source: Anke@FaceBook.com




(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Thursday, January 5, 2012

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ

እስመ ናሁ ተወልደ  ለክሙ ዮም መድኅን ዘዉዕቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዲዊት።
‹‹ዛሬ በዲዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል›› ለቃ ፪፥፲፩
እንኳን ለጌታችንና ለመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በሰላም አደረስዎት!


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, January 1, 2012

Ethiopia The Beautiful


If the sky is bluer Green is the land
And there are no seas, yep there is no sand
Only two month a year it will rain
It's always green, there are no winters pain
the rivers and the lakes are still pure
There is less noise, it's quite for sure
You'll find Anything in Dear Ethiopia
My Beloved country is in the East of Africa
For your vacation Come! it's Paradise
Don't worry about the money go, low is the price
Dear Ethiopia is in the East of Africa
Dear Ethiopia is in the East of Afirca
Colors and Freindship you bet you will find
There's good hospitality & a peace of mind
In Ethiopiaaaaaaa
Pretty girls and boys everyday you can meet
The colors of their xxxxx xxxxxx xxx xx xx
Dear Ethiopia is in the East of Africa
Dear Ethiopia is in the East of Africa
Enat Ethiopia wubituwa hagere
Betam ywedishal Tesfaye Gebre
Enat Ethiopia Wubituwa hagere
Betam ywedishal Tesfaye Gebre
Colors and Freindship you bet you will find
There is much hospitality & peace of mind
In Ethiopia
Pretty girls and boys everyday you can meet
The colors of their blouse black and white
Dear Ethiopia is in the East of Africa
Dear Ethiopia is in the East of Africa
Come Come to Ethiopia
That is my country...Ethiopia Ethiopia 

                                                       Source: Ethiopiananimaiton.com


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)