«ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማሪያም የዐጽብ ለከሉ፤ ሞት ለሟች ይገባል፣ የማሪያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» ቅ. ያሬድ
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በዓል ዕረፍት በሠላም አደረሰን!!!
በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
/ነግሥ ዚቅ፤ የጥር 21 አርኬ/
እመቤታችን በዚህ ምድር ላይ ሦስት ዓመት ከእናት አባቷ ቤት አስራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን ፀንሳ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦሥት ወር ከጌታችን መድኃኒታችን ጋር አስራ አምስት ዓመት ከዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በስድሳ አራት ዓመቷ ጥር 21 ቀን በ 49 ዓ.ም ገደማ አረፈች፡፡
እመቤታችን በዐረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሥጋዋን ሊቀብሩ ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘው ሲሄዱ ለተንኮል የማያርፉት አይሁድ እንዲህ አሉ «ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ ተነሣ እያሉ ሕዝቡን አስኮበለሉ አሁን ደግሞ እናቱን ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያውኩ ሥጋዋን እናቃጥል» ተባብለው ከመሀከላቸውም እንደ ጎልያድ በጉልበቱ የሚመካ ታውፋንያ በሚሉት የጎበዝ አለቃ እየተመሩ ወደ ሐዋርያት መጡ፡፡ ታውፋንያ የተባለው ትዕቢተኛ የእመቤታችን ሥጋ ያረፈበትን አጎበር /አልጋ/ ከሁሉ አስቀድሞ ያዘ፡፡ ወዲያው ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ሁለት እጆቹን በሰይፍ ቀጣው፤ እጆቹም አጎበሩ ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ «እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንም …´ 1ሳሙ. 26-9 ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመናት «የእውነተኛ አምላክ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ ይቅርታ ታደርጊልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ» አላት፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት እንደቀድሞው ደኅነኛ እጅ ሆነለት፡፡
ከዚህ በኋላ መልአክ ዮሐንስን ጨምሮ የእመቤታችንን ሥጋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሩት፡፡ ሐዋርያት «የእመቤታችንን ሥጋ አግኝተን በክብር የምንቀብረው መቼ ይሆን» እያሉ ይናፍቁ ጀመር፡፡
ዮሐንስም ከተመለሰ በኋላ እንደምን አለች? አሉት፡፡ ዮሐንስም «እመቤታችንማ ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ከዚያም ሱባኤው እሑድ ያልቃል እሑድ አምጥቶ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ ማከሰኞ ተነሥታለች «ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ» ያሰኘው ይህ ነው፡፡
ስለ እመቤታችን ትንሣኤ አባቷ ዳዊት በመዝ.131-8 «አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት» በማለት ለአምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ የሆነችው አማናዊት ታቦት ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ልጇ ሁሉ እርሷም ከሙታን ተለይታ እንደምትነሣ ተናግሯል፡፡
ስሎሞንም እንዲህ ብሏታል፡፡ «ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ንይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ÷ ዝናቡም አልፎ ሄደ ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ ÷ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ መዐዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ» /መኃ.2-10-14/፡፡ ይህን ኃይለ ቃል ሲተረጎም በውስጡ ብዙ ምስጢራዊ ነገሮችን ያቀፈ ነው፡-
«በክረምትና በዝናብ» የተመሰሉ የእመቤታችን መከራዋ ናቸው፡፡ ካህኑ ስምዖን «በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል»/ሉቃ.2-35/ እንዳላት፡፡ አሁን ግን ያ የመከራ ክረምትና ዝናብ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ማለፉን ፤
«አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ» ሲል የሐዋርያት ድምፅ ወይም ስብከት በምድር ላይ ሁሉ መሰማቱን ነው፡፡ ዳዊት በትንቢቱ /መዝ.18-4/ «ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ» እንዲሁም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ወደ ዓለም ሁሉ ሒዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ»/ማር.16-15/ ያለው ቃል ተፈፀመ፤
«የዜማ ጊዜ ደረሰ» ዜማ ያለው መከሩን ነው፡፡ መከር የፍሬ ጊዜ ነው ፡፡ ስለሆነም የሐዋርያት ስብከት ፍሬ አፈራ፤
«በለሱ ጎመራ» በጎ ምግባር የሌላቸው ሰዎች ምግባር መሥራት ጀመሩ፤
«ወይኖች አብበዋል መዐዛቸውንም ሰጥተዋል»፡- በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ፣ መዐዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ጀመሩ፣ ወደጄ ሆይ ተነሽ እያለ ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን እንደጠራት በሚያስደንቅ ሁኔታ ሰሎሞን ተናገረው ፤ እመቤታችን በሦስተኛው ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳንጠብቅ በአምላክ ፈቃድ ተነሣች ፡፡
ቶማስ አልነበረም ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት «ወፈቀደ ይደቅ እም ደመናሁ»፡፡ ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ / «ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም»/ዮሐ.20-25-25/ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ ብሎ፡፡ እመቤታችንም «ዐይዞህ አትዘን ወንድሞችህ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም አንተ ዐይተሃል ተነሣች ዐረገች ብለህ ንገራቸው» ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ እርሱ ሔዶ ለሐዋርያት የእመቤታችንን ዕርገት አበሰራቸው፣ ለምልክትም የያዘውን ሰበን /መቀነት/ ሰጣቸው እነርሱም ለበረከት ተካፍለው ወደየ ሀገረ ስብከታቸው ሔደው በዓመቱ ቶማስ ትንሣኤሽን ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው ሱባኤ በነሐሴ መባቻ ገቡ በ16ኛው ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ አቁርቦአቸዋል፡፡
ሞት ለሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ ፈንታ ቢሆንም ከሞተ ሥጋ እናቱን ማስቀረት ሲችል፣ አለማስቀረቱ የፈጣሪ ፈታሒነቱን ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ቅዱስ ያሬድ እመቤታችን የአምላክ እናት ስትሆን ዕረፍቷ የሚያስደንቅ መሆኑን «ሞት ለሟች ይገባል፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት የዘመረው፡፡
የድንግል ማሪያም አማላጅነት አይለየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
No comments:
Post a Comment