Tuesday, August 28, 2012

እናቴ

ከቶ ምን ልክፈልሽ ውዲታ እናቴ
ውለታሽ በዘብኝ ለምስጋና የሚሆን ቃል አጣ አንደበቴ:: 
ከሰው በላይ እንድሆን ያየሽው መከራ
ቢነገር አያልቅም ለአለም ቢወራ፡፡
እራስሽን ጥለሽ እኔን ተንከባክበሽ
ከሰው በታች ሆነሽ እኔን አኮፍሰሽ
ቢያመኝ ተሰቃይተሽ ብሎም ተጎሳቁለሽ
እዚህ አደረሽኝ ከሰው በታች ሆነሽ
ውዲታ እናቴ እግዜር ጤና ይስጥሽ
እኔ በምን አቅሜ በምን ላመስግንሽ፡፡
ውስጤ ተቃጠለ እንባንም አነባሁ
በጣሙን ከበደኝ ውለታሽን ሳየው
እግዜር ዕድሜ  ይስጥሽ ከቶ ምን እላለሁ
ውዲቷ  እናቴ አመሰግናለሁ፡፡
                            ምንጭ:- የወል 

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, August 12, 2012

መሸነፍ ባይኖር ድል ማድረግ ባልነበረ!


ያኔ በባዶ እግር እንዳልተሰበረ፤
ምነው ዛሬ ወገን ሜዳው ባዶ ቀረ።
ያ ቀን እንዳለፈ ይችም ቀን ታልፋለች፤
ኦሎምፒክም ብትሆን ከርሞ ትመጣለች፤
ያ ድል ይደገማል በኢትዮጵያ ልጆች።
ስለዚህ አትሌቶች በተለይ ወንዶቹ፤
እናንት ናችሁና የሀገር ዋኖቹ፤
በርቱ ተበራቱ ሁሌ ሳትሰልቹ፤
ዛሬም ተስፋ አንቁረጥ የአበበ ዘሮቹ።
መሸነፍ ባይኖር ድል ማድረግ ባልነበረ!
አቤም በባዶ እግሩ ሮምን ባልዞረ፤
የአበበንስ ታሪክ ማን በመሰከረ፤
ስለ ኢትዮጵያ ማንስ በዘከረ፤
ግና በመሸነፍ ጅርባም ማሸፍ ስላለ፤
አቤ ታሪክ ሠራ በባዶ እግሩ እያለ፤
ዓለም እስከ ዛሬ ስለኢትዮጵያ ሲመሰክር ኖረ።
እስኪ እንጥይቃቸው ምን ነበር ታሪኩ፤
ምንስ ይዘው መጡ እን ኃይሌ ሲላኩ።
ይቻላል ይል ነበር ጅግናው አትሌት ኃይሌ፤
አሁንም ይቻላል አንሁን ባተሌ፤
እንደ አባት ይምከረን ኃይሌም ቢሆን ሁሌ።
እናም አትሌቶቹ የሀገር ዋኖቹ፤
የኢትዮጵያ ልጆች የአበበ ዘሮቹ፤
ያ ቀን ይመለሳል አሁንም አትሰልቹ፤
ታሪክ ይደገማል አሁንም አትሰልቹ።

ማስታወሻነቱ፦ በነሐሴ 6/2004 ዓ.ም. ለታጣው የማራቶን የኦሎምቲክ ድል፣ በውድድሩ ለተሰለፉት አትሌቶች እና ለመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን አበበ ቢቄላ ይህንልኝ። 
አለምነው [ነሐሴ 6/2004 ዓ.ም.]


(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Saturday, August 11, 2012

ታዘብኳችሁ!



ወገኔ ምን ነካችሁ?
እንዲያው በብዙ ታዘብኳችሁ።
ፌስቡክን መሉ እንዳልነበር ጩኸታችሁ፤
ኢሜል ሙሉ እንዳለነበር ድጋፋችሁ፤
ብሉግ ሙሉ እንዳልነበር እልልታችሁ፤
ታዲያ ትናንት ምን ነካችሁ?
እንዲያው በብዙ ታዘብኳችሁ።
ሥዕል አድህኖ ስላያችሁ?
ደግሞም ምትሃት ነው ትላላችሁ፤
ለማን ነው ይሆን ድጋፋችሁ?
ለአትሌቶቹ ወይስ ለኢትዮጵያ ለሀገራችሁ ።
ለማን ይሆን ወርቁ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለመሰረት?
ለማን ይሆን ስሙ? ለኢትዮጵያ ወይስ ለመሰረት?
አቋማችን አንድ ይሁን ለዓላማ ለአንድነት፤
ጹኑ አቋምም ይኑረን አንድ ኢትዮጵያዊነት።
ወርቁም ቢመጣ ለኢትዮጵያ ነው፤
ሥሟም ቢጠራ ኢትዮጵያ ነው፤
ታዲያ ወገኔ ሽሙጡ ምንድን ነው?
አዎ! መሰረትም ላቧ ጠብ ያለበት ደምወዟ ነው፤
ያም ሆነ ይህ ክብሩ ግን ለኢትዮጵያ ነው።
እናም ወገኔ አትሸወድ፤
አንዱም በአንዱ ላይ አይፍረድ፤
ድጋፋችን ከሰው ብቻ ወደ ኢትዮጵያም ይውረድ።
አዎ! ታምናለች፣ ያመነችበትንም ሰርታለች፤
ታዲያ መሰረት ምን አጠፋች?
ሥዕል አድህኖ ስላሳየች፤
ጣኦት አምላኪ ተባለች።
ግን ይህ አይደለም አምልኮ ጣኦት፤
ለቆሙበት አላማ ያመኑበትን መስራት፤
ደግሞም ከሁሉ በአምላክ እናት።
ታዲያ ለምን ነው ይህን ያክል ሽሙጡ፣
በውስጠ ወይራ ቃላትን ልውውጡ።
አዎ! አትሌቶቻችን ናቸው የእኛ ሞገስ የኛ አርዕያ፤
አዎ! አትሌቶቻችን ይገባቸዋል ክብር፣ ስለሆኑ ለኢትዮጵያ ማስጠሪያ፤
ድጋፋችን ግን ለሰው ሳይሆን ይሁን ለኢትዮጵያ።
ለአትሌቶቻችን እስኪ እንስጣቸው ሞራል፤
ክብር ለሚገባው ክብርም ቢሆን ይገባል።
ታዲያ ወገኔ ለምን አላደረግንም ይህን?
ፍቅራችንስ፣ ከአንገት በላይ ለምን ይሆን?
ፉጨታችን ለሰው ብቻ ለምን ይሆን?
ምን አመጣው  ሃሜትን?
ያየነው ባህሪ ከዘወትር ስለተለየብን፤
ወገኔ አትሳሳት ድጋፍክም ቢሆን፤
ለሀገር እንጂ ለሰው ብቻ አይሁን።
ታዲያ ወገኔ ምን ነካችሁ?
ፍቅራችሁንም ቀነሳችሁ?
እኔስ በብዙ ታዘብኳችሁ።
እንዲህ ነበር ወይ ወጉ፤
ላሸነፈ ሽልማቱ፣ ወርቅ ላመጣ ማዕረጉ፤
አቤት ባየን መለስ ብለን ከአባቶቻችን፤
ብናነብስ ብንጠይቅስ ምን እንደነበር ታሪካችን፤
ፍቅር እንጂ ማማት አልነበረም ባህላችን።
ተው ወገኔ ቆም ብለህ አስብ፤
ታሪክህንም ጠይቅ አንብብ፤
ከደመቀው አትዝፈን፤
እርስ በርስህ አትጨክን፤
ለኃጥአን የመጣው ለጻድቃን እንዳይሆን፤
ፍቅራችንም ከአንጀት እንጂ ከአንገት አይሁን።
እናም ወገኔ! እናስተውል፤
ዛሬ ብንተዛዘብ ቀንም ያልፋል፤
የጭንቅ ቀንም ይመጣል፤
ታዲያ ያኔ ምን ሊባል?
ጥሩነሽ ብቻ ትሩጥ አይባል፤
አይቀርም እኮ በመሰረት አደራ መጣል።
ስለዚህ ወገኔ ተጠንቀቅ፤
የምትናገረውን የምትጽፈውንም እወቅ፤
ከዚያም ይሆናል የተባረከ ወርቅ።
አለዚያ ግን ወገኔ፤
እንደታዘብኩህ እኔ፤
ጩኸት እንጂ የለምህም ወኔ።

ማስታወሻነቱ፦ ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል በቅ.ድንግል ማሪያምን ስዕለ አድህኖ ላይ እምነቷን በመግለጿ ሳያውቁ ሽሙጥን ላበዙባት ድል አድራጊዋ መሰረት ደፋር
አለምነው [ነሐሴ 5/2004 ዓ.ም.]









(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Friday, August 10, 2012

ማለዳ ሲቀና እስከ ማታ ጤና!



ማለዳ ሲቀና እስከ ማታ ጤና!
 ዛሬም ተደገመ! በራስ መተማመን መሰረት ነውና።
 እምዬ ኢትዮጵያ ስንት ልጆች አሉሽ?
 እንደ ንብ ተናድፈው በዓለም ያስጠሩሽ፤
እንደ አንበሳ ታግለው ወርቅም ያመጡልሽ፤
ቁጥራቸው ብዙ ነው ፍቅርን ያድልልሽ።
በባዶ እግር ተሩጦ ተጥሎ መሰረት፤
ዛሬም ወርቅ አገኘን በአምላክ ቸርነት።
ባንዲራውም ከፍ አለ፣
መዝሙርሽም ተዘመረ፤
እንደ ሁሌው ተጨፈረ።
አንቺ ሀገሬ፣ ልጆችሽ ናቸው መንፈሰ ብርቱ፤
አንዲቱ ብትቀር ሌላይቱ፣
አልበገርም ባይነቱ፣
ወርቅን አስገኘሽ ዛሬም እንደ ጥንቱ፤
ሁሌም አይቀር ስምሽም መጠራቱ። /2/
 የታደልሽ ሀገር ሥመ ጥሩ፤
ልጆችሽ ደፋር ሞት አይፈሩ፤
ይኖራሉ ዘላለም ስምሽን ሲያስጠሩ።
ይህ አይደለም እንዴ የአባቶሽ ብሒል፤
ከቤት ዶሮ ሲታረድ ከሜዳ ቆቅ ይገባል፤
ገና ይደገማል! ስምሽም ለዘላለም ይጠራል።
ሲታገሉ ውሎ ሲስቅ አዳሪ፤
የእናት ሀገሩን ስም በዓለም አስጠሪ፤
አምላኩን የፈራ ሰውንም አክባሪ፤
 ብቃቱን በሥራ በሰው አስመስካሪ፤
 መሰረት ጥሩነሽ ቀጥይበት ሥሪ። /2/ 

ማስታውሻነቱ፡- ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል እና ድል አድራጊዋ መሰረት ደፋር
አለምነው [ነሐሴ 4/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

Sunday, August 5, 2012

አዎ ይደገማል!

አዎ ይደገማል!

አዎ ይደገማል!
እማማ ኢትዮጵያ ኩሪ ይገባሻል፣
እንደ ቲቂ ያሉ ልጆችን ወልደሻል። 
ወርቅማ ወርቅ ነው፣ በብርም ይገዛል፤
ይህን ክቡር ስምሽ ከቶ ማን ያስጥራል፤ 
ልጆችሽ እያሉ ዘላለም ይጠራል፣ አዎ! ይደገማል። 
ገና መች ተነካ አዎ ይደገማል! 
እማማ ኢትዮጵያ ክብር ለባንዲራሽ፤
ሰላም ለልጆችሽ፣ አምላክ ያድልልሽ፤ 
ስምሽን አስጠሩት ወርቃማ ልጆችሽ። 
ሁሉም በአንደበቱ ቲቂ ቲቂ እያለ፤
በልቡም አምላኩን እርዳቸው እያለ፤
ሰዓቱም ተገፋ፣ ርቀቱም አጠረ፣ 
ኮመንታተሩ ሳይቀር ገላና ገላና ከኢትዮጵያ እያለ፤
ቲቂ ብቅ ስትል፣ እልልታው አየለ። 
አዎ ይደገማል! 
ስምሽም ዘላለም በአለም ይጠራል። 


ማስታውሻነቱ፡ ሐምሌ 29/2004 ዓ.ም. ለተገኘው የማራቶን ድልና ድል አድራጊዋ ቲቂ ገላና።

አለምነው [ሐምሌ 29/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

እውነትም ጥሩነሽ

እውነትም ጥሩነሽ

ጠላትሽ በሙሉ ውድቀት ቢመኝልሽ፤
አንቺ ግን አንቺው ነሽ፣ ሁልጊዜም ጥሩነሽ፤
ቤቢይ ፌስ ኪለሯ፣ እወነትም ጥሩ ነሽ።
ትንሹም ትልቁም ህጻን ልጅ አዋቂው፤
በውስጥም በውጭም ባህር ማዶም ያለው፤ 
ጥሩነሽ እያለ ልቡንም በተስፋ ቢሞላው፤
ወርቁም አልቀረበት ኩራትም ተምሰማው፣ ባንዲራውን ሲያየው፤
ያ! ሰው ወዳድ ወገንሽ፣ መክሮ ያሳደገሽ፤ 
ሁሉም ደስብሎታል፣ አንቺም ደስ ይበልሽ። 
እማማ ኢትዮጵያ፣ ልጆሽ የት አሉ? 
እንደነ ጥሩነሽ፣ እንደ ቀነኒሳ፣ እንደ ኃይሌ ያሉ፤
ወርቁማ ወርቅ ነው ስምሽን ያስጠሩ። 


ማስታወሻነቱ፡ በሐምሌ 27፣ 2004 ለተገኘው የኦሎምፒክ ድል እና ድል አድራጊዋ ጥርነሽ
አለምነው  [ሐምሌ 27/2004 ዓ.ም.]

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)