Monday, December 24, 2012

ጨንጓራ ስምሽን ለውጠሽ መጣሽ?

       (አለምነው ሽፈራው)፦ አንድ የኔ ቢጤ ምስኪን የሀገሬ አርሦ አደር ወደ ከተማ ጎራ አለና  ምግብ ፍለጋ ወደ አንድ መጠነኛ ምግብ ቤት ገባ። እንደገባም የምግብ ቤቱ አስተናጋጅ ምን ልታዘዝ አለው። ያ ምስኪን አርሦ አደር ምን ምን አለ ሲለው፤ አስተናጋጁ በግርግዳው ላይ የተለጠፈውን የምግብ ዝርዝር አሳይቶ ምረጥ ብሎት ዞር አለ። በዝርዝሩ ውስጥም «ዱለት» የሚል አየና፣ ዱለት አዘዘ። ምግቡ ተሰርቶ ሲቀርብለት፣ ሲያይ  እርሡ የሚያውቀው ጨንጓራ ነው።  ከዚያም «አይ ጨንጓራ ስምሽን ለውጠሽ መጣሽ» አለ። ይህን ስል እንዲሁ ለቀልድ እና ለጨዋታ ብቻ አይደለም። ለቁም ነገር እንጅ። 
ዛሬ ዛሬ ተሐድሶዎችም ልክ እንደ ጨንጓራ ስም እየለወጡ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እስከ አሁን እነ አባሰላማ፣ አውደምረት፣ እና የመሳሰሉት የተሐድሶ መናፍቃን የጡመራ መድረኮች ክብር ይግባዉና መድኃኒታችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ፣ ልመናዋ አማልጅነቷ ይሰማል እንጂ እንዲሁ የማይቀርን እመብርሃን ድንግል ማሪያምን አታማልድም፣ ቅዱሳንን አያማልዱም፣ ገድላት ድርሳናት ልብ ወልድ ናቸው በማለት ሲዘባበቱ፣ ቅድስት አንዲት የሆነች በጌታችን ደም የተመሰረተች ኦርቶዶክሳዊት  ቤተክርስቲያናችንን ያረጅች ያፈጀች ናት በማለት ሲኮንኑ፣ እንዲሁም ብጹዓን ጳጳሳት አባቶቻችንን፣ በገዳም ያሉ አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን፣ ትጉህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን እና ማኅበራትን ያለ ስሙ ስም በመስጠት  ንጽህት ቅድስት የሆነች አንዲት ሃይማኖታችንን ለማፍረስ የምይፈነቅሉት ድንጋይ የማይምሱት ጉድጓድ የለም። አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ።  የቤተ ክርስቲያንን ልጆችም ለመንጠቅ ጥንብ እንዳየ አሞራ እያንጃበቡ ይገኛሉ። 

አሁን አሁን ምዕመናን፣ የቤተክርስቲያን ልጆች አላማቸውን አውቀውባቸው ራሳቸውን እና ሃይማኖታቸውን ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ፤ እንዲሁም  የነሱን የሐሰት በሬ ወለደ መረጃዎች የያዙትን የጡመራ መድረኮቻቸውን  ከማንበብ ሲቆጠቡ ስም እየለወጡ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።  ዛሬ ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ አጀንዳ የሆነውን የእርቀ ሰላም ጉዳይ እና የፓትርያሪክ ምርጫ በሆነበት ወቅት፣ ያልሆነው ሆነ፣ ያላዩትን አየን፣ ያለሰሙት ሰማን እያሉ፣ ጫፉን ይዘው ሲጎትቱ (ትክክለኛውን መረጃ ሳያገኘት ማለቴ ነው) ወሬ በማናፈስ ላይ ይገኛሉ።  አላማቸው አንድ እና አንድ ነው። በውሸት ተዋህዶን ለማጥፋት። መስሏቸው ነው እንጂ እርሷስ አትጠፋም፤ በአለት ላይ ተመስርታለች እና። 

ሲጅምሩ ቲፎዞ ለማፍራት፣ የአንባቢያንን ቁጥር ለመጨመር ኦሮቶድክሳዊ ይዘት ያላቸው ዜናዎችን፣ መረጃዎችን ማስነበብ ይጀመሩና ቀስ በቀስ ደግሞ ሸተት ሸተት ይላሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ «ተሐድሦ ሆይ ስምሽ ለውጠሽ መጣሽ?» ማለት ይገባል። 

መጽሐፍ ቅዱስ «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ። ፩. ተሰ. ፭፥፳»  ብሎ እንደሚነግረን  እኛም የምናነባቸው መረጃዎችን ምንጫቸውን ጠንቅቀን መመርመር ያስፈልጋል።  መልካሞችን መያዝ፣ ላልሰማም ማሰማት፣ ላልደረሰው ማዳረስ ( በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በፌስ ቡክ፣ በጐግል ፕላስ፣ በትዊተር..) ያስፈልጋል። አንዱ የሀገራችን አርቲስት (የሰው ለሰው- አስናቀ ማለቴ ነው)  «መረጃ አይናቅም አይደነቅም» አይደል ያለ። አዎ! እውነት ነው መረጃ አይናቅም አይደነቅም።  
«ጀማሪ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል» እንደሚባለው እነዚህ አቋማቸውን በውል ያለዩ የጡመራ መድረኮች ጥፋታቸው ከቀደምቶቹ የበለጠ ነው። የቀደምቶቹማ ታወቀባቸው፣ ተነቃባቸው። እነዚህ ግልግሎቹ ግን ወሬ ለማራገብ ማን ይሆናቸዋል?  
ሌላው የእነዚህን የተሐድሦ መናፍቃን የጡመራ መድረኮች  ሸር ማድረግ፣ ላይክ ማድረግ ለነሱ አንድ ጥቅም ያስገኛል። እርሡም በአብዛኛው ሁሉም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚጠቀሙት ስልት ለጓደኛ ጓደኛህ እንዲህ ሰራ፣ ይህንን ወደደ/ ላይክ አደረገ/  ወ.ዘ.ተ. በማለት ወሬውን በቶሎው ያደርሳሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ እነዚህን የሐሰት የመረጃ ቋቶች እና መድረኮች ላልሰማው፣ ላላየው እያሳወቅን በያዙት ሃሳብ እንዲጨነቅ፣ እንዲሁም ደግሞ እውነት ይሆንን እያለ እንዲጠራጠር (ብዙም እውቀት የሌለው ከሆነ ማለቴ ነው)  ያደገዋል።  እንዲሁም አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል አንድ እንደ አርአያ የሚቆጥረው ሰው አንድን ሥራ ሰርቶ ካየ ትክክል ነው ብሎ የመቀበል ዝንባሌው ያመዝናል። በዚህም እኛ ሸር፣ የምንወዳቸው  (በፌስ ቡክ ቋንቋ ላይክ) የምናደርጋቸው የጡመራ መድረኮችንም እንዲሁ እኛን የሚያዩ የዋሆች ይቀበላሉ። መጥፎ ሀሳብ ያላቸው ከሆነ ሳያውቁት ወደ ገደል እየመራናቸው ነው። መልካም ከሆነ ደግሞ በተቃራኒው። 
ታዲያ ይህ  መልካም ሥራ የምንሠራበትን ውድ ጊዜያችንን በመጨነቅ ማሳለፋችን፣ ብዙ እውቀት ለሌለው ደግሞ መጠራጠሩ ለተሐድሦአዊያን ትርፍ አይደለምን? ያውም ምንም ሳይሰሩ ያገኙት ትርፍ። ሥለዚህ የነሱን አንብቦ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማዳረሱ ጉዳቱ አደገኛ ነው እና እንወቅበት። 
ዲ.ን ኤፍሬም እሸቴ አደባባይ በተባለው የጡመራ መደርኩ «ከዜግነታዊ ጋዜጠኝነት አንዱ ጡመራ» ነው ብሎናል። እውነትን ይዞ መጦመር  ዜግነታዊ ጋዜጠኛ ያስብላል።  ቅሉ ግን በሀሰት ወሬ በማሳበቅ ሰውን ለማደናደናበር መሞከር ወንጀል ነው፣ ያስቀጣልም።  ጦማሪያንም አቋማችንን እንለይ።

«መጦመር እንጅ መቆመር ይቅር»

(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)

መልክአ ኢትዮጵያ

የድንግል ማሪያም የአሥራት ሀገር፤ የብዙ ቅዱሳኑ መጠጊያ፤ ሀገረ እግዚአብሔር ቅድስት ኢትዮጵያ። 
መልክአ ኢትዮጵያ

ሰላም ለዝክረ ስምኪ ኢትዮጵያ
ሀገሩ ለተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ፤ 
 ህዝብኪ ይዜምሩ እንዘ ይብሉ ሃሌ ሉያ።
 የሃይማኖት ድር የዉበት መለያ፤ 
ቀደምት ባለ ታሪክ የዓለም አርአያ።  

ሰላም ለአይንትኪ እለ ርእያ ፈጣሪ፤
ታምረ ኩሉ ገባሪ። 
ማዳን ፍቅሩን ላዩ፤
ከጸሎት ላልዘገዩ። 

ሰላም ለአእዛንኪ እለ ሰምዓ ፈጣሪ፤
በከመ ኮነ እግዚአብሔር መሐሪ፤
ቅዳሴው ሰዓታቱ፤
ላደመጡ ማኅሌቱ።
ሰላም ለአፉኪ ዘነበበ ወንጌሉ፤
እንዘ ይፌጽም ቃሉ፤
ሃሌሉያን ለለመደ፤
አኰቴትን ለወደደ፤
ቅኔ ዜማን ላወረደ። 

ሰላም ለገጽኪ ለለብሰ ልምላሜ፤
መልዓ ምሥጢር ወትርጓሜ፤
ለማይሽረው ዘመን እድሜ፤
የመልከኛ ሥያሜ፤
ለሆነው የውበት ፍጻሜ። 


ሰላም ለሀዳፍኪ እለ ሰፋ ሀበ እግዚአብሔር ህያው፤
ጸሎቱ እና ሙያው፤
ውዳሴ ነውና ግብሩ፤
ጌታሽ ነውና ክብሩ። 

ሰላም ለከርስኪ ዘአስረጸ ማዬ፤ 
ለጸሙ ሰብ ዘአስተዬ፤
ቅዱሱ ጸበል ለፈቀበት፤
የቅዱሳኑ አጽም ላረፈበት፤
ፈዋሹ እምነት ለተገኘበት።

ሰላም ለዘባንኪ እምዘባነ አለም ዘተሌለዬ፤
ጸዊረ ተሰዓቱ ቅዱሳን በሰቢከ ወንጌል ዘአብ፤
እንግዳን መቀበል ላልደከሙ፤
መካናትሽን ለተሸከሙ። 

ሰላም ለወልድኪ ያሬድ ማኅሌታይ፤
ወጣእመ ዜማ ቀዳማይ፤
 ግዕዝ እዝል ወአራራይ።
ምድርሽን በዝማሬ ላራሰ፤
የአፉን ቅኔ ላፈሰሰ። 

ሰላም ለወልድኪ አባ ተክለ ሃይማኖት
 ዘሖረ በሰናይ ፍኖት፤
እንደ መላእክቱ በክንፍ ለበረረ፤
ባከበረው ንጉስ ለከበረ፤
ጣዖታትን ለሰበረ።

ሰላም ለወልድኪ አባ ዜና ማርቆስ፤
ሐዋርያሁ ለክርስቶስ፤
እምዘመደ ተክለ ሃይማኖት ባህታዊ፤
ጥሪው ሰማያዊ፤
መንገዱ ሰላማዊ። 

ሰላም ለወለትኪ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ፤
እንበለ መጠን ዘበስዓ እበያ ወክብራ፤
ለተመሰገነች በጽድቅ ሥራ፤
እጅ ላልሰጠች ለዓለም ምርኮ፤
ለጸናች በአምልኮ። 

ሰላም ለመካንኪ ግሸን ደብረ ከርቤ፤
ለይዜምሩ ካህናት በፍሥሐ ወበይባቤ፤
ፍኖተ ብርሃን ይእቲ፤
 መንበረ መስቀሉ ዛቲ፤
መግቢያ በሯ አሐቲ። 

ሰላም ለመካንኪ መካነ ቅዱሳን ዝቋላ፤
እንተ ጸለዬ በአንቲ ገበረ መንፈስ ቅዱስ በማዕከላ፤
የቅዱሳኑ መፍለቂያ፤
የሰዓታቱ መድመቂያ።

ሰላም ለመካንኪ እንተ ተሰይመት ጻድቃኔ፤
በአት ይእቲ ለመናኔ፤
የድውያኑ መፈወሻ፤
የሀዘንተኞች ጭንቅ መርሻ፤
የዲያቢሎስ ድል መንሻ። 

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ላሊበላ፤
መካነ ትብስእት ወተድላ፤
የጸጋው ዘይት ሲፈላ፤
የተቀባው ልጅሽ፤
 ላነጸው መቅደስ በደጅሽ። 

ሰላም ለመካንኪ መርጦ ለማርያም፤
ደብረ ምሕረት ወሰላም፤
ለማይቋረጥባት እንጣኑ፤
ለሚጸልዩባት ቅዱሳኑ፤
ለፈለቁባት ምሁራኑ።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ዮሐንስ ሸንኮራ፤
እምነ ውስቴታ ደናግል ዘይዜምራ፤
ጸበሉ እውራንን የሚያበራ፤
የዮሐንስ ገዳም የመጥምቁ፤
የዘካርያስ ልጅ የጻድቁ።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ጽዮን አክሱም፤
እንተ ሀለወ ባቲ ታቦተ ጥንታዊት ወቅድም፤
ለጽዮን መኖሪያ ለከበረችው፤
ዳጎንን ለሰበረችው፤
ዳዊትን ካባ ላስጣለችው።

ሰላም ለመካንኪ ዋልድባ ሰላማዊት፤
አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፤
የአባ ሳሙኤል ገዳማቸው፤
ለሚተረክባት ገድላቸው፤
ላከበራት ጸሎታቸው።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ አሰቦት ቅድስት፤
መካነ ቡሩካን ውድስት፤ 
ጸሎት ላልራቃት ጠዋት ማታ፤
ለቀደሳት ጌታ።

ሰላም ለመካንኪ ደብረ ሊባኖስ ገዳሙ፤
እንተ አእረፈ ባቲ ለተክለ ሃይማኖት አጽሙ፤
ቅዱሱ ደብር መታሰቢያ፤
የመናንያን መሰብሰቢያ፤

የባለ ቅኔው ማሸብሸቢያ።

ሰላም ለመካንኪ መካነ ሰላም ደብረ ዳሞ፤

ይጸልዩ ባቲ አበው ቅዱሳን በአርምሞ፤
አረጋዊ በዘንዶ፤
በገደል ላይ ተረማምዶ፤
ለገደማት ጌታ ፈቅዶ።

ሰላም ለመካንኪ ምስራቀ ፀሐይ ዘደብረ ዘይት፤
መካነ ሕይዎት አማናዊት፤
ላሳደገችን በውብ ቋንቋ፤
ላስያዘችኝ የዜማ ቃል። 

ሰላም ለአቡኪ ወልደ ማርያም፤
ንጉሰ ነገስት ስቡህ በአርያም፤
ጠላትሽን ለተዋጋ፤
ለብርታሽ ክንዱን ለዘረጋ፤
ቅጥርሽን በእሳት ለዘጋ።

ሰላም ለእምኪ እመ ብዙኃን፤
ዛቲ ይእቲ ተድላ ብዙኃን፤
በአሥራት ለተሰጠሻት፤
በየዘመን ለጠራሻት፤
ስለ ፍቅሯ እናት ላልሻት። 
መልክአ ኢትዮጵያ። 






(ወደሚቀጥለው ገጽ ይዞራል Read More)